የአሰልጣኞች አስተያየት | አዲስ አበባ ከተማ 4-3 ሰበታ ከተማ

አዲስ አበባን ባለ ድል ካደረገው እና ሰበታ ከተማ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ተያይዞ መውረዱን ካረጋገጠበት ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው – አዲስ አበባ ከተማ

ስለድሉ

“ከዕረፍት በፊት በጥሩ መንገድ ሄደናል፡፡ ከዕረፍት በኋላ ግን ትንሽ ያው ዝናቡ ጨዋታ አበላሽቶብኛል ብዬ እገምታለው፡፡ ምክንያቱም እንደተመለከታችሁት ሜዳው ከዕረፍት በፊት ለመጫወት በጣም ይመች ነበር፡፡ ከዕረፍት በኋላ ግን አይመችም ነበር። አንድ እሱ ፣ ሁለተኛ ደግሞ ይሄን ውጤት ከመፈለግ እኛ የምንፈልገውን ጨዋታ ተጫውቻለሁ የሚል ግምት በእኔ አመለካከት የለም፡፡

ጥንቃቄን አለመምረጣቸው

“ምንም የሚያወላዳ ነገር የለም፡፡ እነርሱም የሆነ ጭላንጭል ለማየት ማሸነፍ ነው፡፡ እኛም ማሸነፍ ነው፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ማሸነፋችን ምን ላይ እንደሚያደርሰን ከተጫዋቾቼ ጋር በደንብ ተማክሬያለሁ፡፡ ይሄን ቡድን ከተረከብኩት አንድ ወር ነው። ምን ላይ መስራት አለብኝ የሚለውን ነገር ከልጆቹ ኳሊቲ በመነሳት ነው የምትሰራው፡፡ ከዚህ ውጪ ከወጣህ ቡድንህ ይበላሽብሀል፡፡ የራስህን ነገር ሰራለሁ የምትለው በሚቀጥለው ዓመት በሰፊው ስታገኛቸው ነው እንጂ ብዙ ስህተት እንዳሉ እነዛን ለመቀነስ ነው ትልቅ ትግል ያደረኩት፡፡ እንደውም እስከ አሁን ለመውረድ መቆየት የለብኝም ነበር፡፡ ከያዝኩኝ ጀምሮ ቡድኑ እስከ አሁን ሽንፈት አልገጠመውም ፤ ከአቻ ውጤቶች ውጪ፡፡

በቀጣይ በቅጣት ስለማይኖረው ሪችሞንድ ኦዶንጎ

“እኔ በእዚህ ዓይነት ነገር ከዚህ በፊትም ብያለሁ፡፡ እኔ ኮከቦች የሉኝም ሀያ አምስቱም ኮኮቤ ነው፡፡ የዛን ቀን ደግሞ ሌላ ሰው በዕርግጠኝነት ታያላችው እንደዚህ ዓይነት ዕምነት አሰልጣኞች ካለንማ ቡድናችን ይበላሻል፡፡ በዚህ ዓይነት ነገር ብዙ የሚያስጨንቀኝ ነገር የለም፡፡ ሁሉም የሰራ ፣ ፊዚካሊ ፊት የሆነ ይጫወታል ስለዚህ ብዙ አያሳስበኝም፡፡

ስለ ቀጣይ ሁለት ጨዋታዎች

“እዚህ ያደረሰ አምላክ የትም የሚወረውረን አይመስለኝም፡፡ እንደ ፈጣሪ ፍቃድ መቶ ፐርሰንት ፕሪምየር ሊግ ላይ እንቆያለን፡፡”

አሰልጣኝ ብርሀን ደበሌ – ሰበታ ከተማ

ከሊጉ ስለመውረዳቸው

“የዚህ ዓመት ውድድር ከጅምሩ ብዙ ትግል የነበረው ነው፡፡ መጀመሪያ የጣልናቸውን ነጥቦች ከቅርቃር ውስጥ ለማውጣት እጅግ ፈታኝ የሆኑ ስራዎችን ስንሰራ ነበር፡፡ በዚህ ሥራ ውስጥ ቡድኑን ከፍ ለማድረግ የተወሰኑ ውጤቶችን አምጥተናል፡፡ ነገር ግን በምናስበው ልክ ስላልሄደልን ቡድናችን የመውረድ ዕጣ ፈንታ ሊገጥመው ችሏል፡፡

ከአስራ አምስት ዓመት በላይ በክለቡ ውስጥ ስለ መቆየታቸው

“ትንሽ ደስ የማይል ስሜት ተሰምቶኛል፡፡ ምክንያቱም ይህ ክለብ ትልቅ ክለብ ነው፡፡ የተወሰኑ ውስብስብ ችግሮች ነበሩ፡፡ እንደ ሥራችን ከሆነ ይህ ቡድን ከፍተኛ ካሉት ክለቦች ተርታ መሆን የሚገባው ነገር ግን በዚህ ጨዋታ ትንሽ ሀዘን ተሰምቶኛል፡፡ ነገር ግን ክለብ ነውና ለሚቀጥሉት ደግሞ ጠንካራ ሆኖ ተሰርቶ ወደ ላይ የሚመጣበትን ሁኔታ ማሰቡ የተሻለ ነው፡፡ ቀጣይ ሁለት ጨዋታዎችን ተጫውተን በጥሩ ሥነ ምግባር ውድድራችንን እንጨርሳለን፡፡

በአስር ዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ መውረዱ እና ስለ ቀጣይ ተስፋው

“አስር ዓመት ከዚህ በፊት የቆየበት ሁኔታ የራሱ የሆነ ችግሮች አለበት፡፡ አሁን ግን ያን ሁኔታ ይቆያል የሚል ዕምነት የለኝም ፣ ምክንያቱም ከነበሩት ችግሮች የተለያዩ መፍትሔዎችን ማስቀመጥ የሚቻልበት ወቅት ነው፡፡ የዘንድሮው አመት አስተማሪ የሆነ ለዚህ ክለብ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ክለቦችም ነው። ይሄ መውረድ እጅግ ስሜት የሚነካ ነው፡፡ ምክንያቱም የመጣበት መንገድ ከስምንት ዓመት በኋላ ወደ ላይ ሲወጣ አብሬው ነበርኩ ከክፍሌ ቦልተና ጋር ይዘነው ነው የወጣነው ምን አይነት ፈተና እንደገጠመን እናውቃለን፡፡ ይሄ ክለብ ደግሞ መውረድ የማይገባው ነበር፡፡ በጥቃቅን ስህተቶች በተለያዩ ውስብስብ ችግሮች ነው የወረደው እንጂ እንደተሰራው ቢሆን ይሄ ክለብ እዚህ ደረጀ የሚገባው አልነበረም፡፡”