አሠልጣኝ ካሣዬ አራጌ ውላቸው ከዛሬ ጀምሮ ይቋረጣል

አሠልጣኝ ካሣዬ አራጌ ቀሪ የአንድ ዓመት ውል እያላቸው በውሉ ላይ በተቀመጡት ዝርዝሮች መሠረት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ከዛሬ ጀምሮ እንደሚለያዩ ሥራ-አስኪያጁ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ተናግረዋል።

የ2003 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ባለቤት የሆነው ኢትዮጵያ ቡና ነሐሴ 30 2011 ላይ የቀድሞ ኮከቡን ካሣዬ አራጌ ለአራት ዓመት በሚቆይ ውል ማስፈረሙ ይታወሳል። አሠልጣኙ በመጀመሪያው ዓመት ያለ ገደብ ከሰራ በኋላ በቀጣዮቹ ዓመታት ከ1-3ኛ ደረጃ እንዲወጣ ግዴታ የተጣለበት ውል እንደተፈፀመም በወቅቱ በተሰጠ ዘለግ ያለ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተጠቅሶ እንደነበር አይዘነጋም። ክለቡ ዓምና በሊጉ ሁለተኛ ቢወጣም ዘንድሮ ግን በ42 ነጥቦች 6ኛ ደረጃን ይዞ ፈፅሟል። ይህንን ተከትሎ የአሠልጣኙ ውል ይቋረጣል የሚሉ ጉዳዮች ከሰሞኑን ሲሰሙ የቆዩ ሲሆን የክለቡ ሥራ-አስኪያጅ ገዛኸኝ ወልዴ ረፋድ ላይ በኢትዮ ስፖርት የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ በእንግድነት ቀርበው የሰጡት አስተያየት የአሠልጣኙ እና የክለቡ የእህል ውሃ ከዛሬ ጀምሮ እንደሚቋረጥ ይጠቁማል።

ውሉ ላይ በተቀመጠው መሠረት አሠልጣኙ ከክለቡ ይለያያል ወይ የሚለውንም ጥያቄ የክለቡ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ በደፈናው “በውሉ መሠረት ከሄድክ ይሄ ነው የሚሆነው” ብለው ሲመልሱ ተደምጧል። በንግግራቸው አሠልጣኙ ከዛሬ ሰኔ 30 በኋላ ከመንበሩ እንዲነሳ ተደርጎ በምትኩ የሚመጣውን አዲስ አሠልጣኝ በተመለከተ ደግሞ “መስፈርቱ ውጤትም መሆን አለበት ሁለተኛ ደግሞ የክለቡንም ቀለም ማስቀጠል ያለበት አሠልጣኝ ነው የሚሆነው ብለን ነው የምናስበው። ኢትዮጵያ ቡና ከበርካታ አሠልጣኞች ጋር ስሙ ተነስቷል። አንድ ብቻ ሳይሆን በርካታ አሠልጣኞችን አነጋግረናል። እንደጨረስን በቅርቡ ለመላው ደጋፊዎቻችን አሠልጣኙን ይፋ እናደርጋለን።” ብለዋል።

በተያያዘ ትናንት እና ዛሬ ከክለቡ ጋር ስማቸው የሚነሱ ተጫዋቾችን በተመለከተ አቶ ገዛኸኝ “በነገራችን ላይ ቴክኒካል ቡድን አለን። ይሄ ቴክኒካል ቡድን የትኛውም ሀገር ላይ የአሠልጣኝ ክፍተት በሚኖርበት ጊዜ ይመጥናሉ እና ክለቡን ያጠናክራሉ የሚላቸውን ተጫዋቾች ያመጣል። ይሄንን መሰረት አድርገህ ወደ ውይይት እና ንግግር ትገባለህ። በመጀመሪያ ደረጃ የሚደረጉ ንግግሮች ሁሉ ተግባራዊ ይደረጋሉ ማለት አይደለም። መነጋገር እና መፈረም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። እያነጋገርናቸው ያሉ ተጫዋቾች አሉ። ነገርግን በይፋ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ነው የሚባሉት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተገኝተው ፊርማቸውን ሲያኖሩ ነው።” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።