የጣና ካፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊደረግ ነው

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እና ጎፈሬ በጋራ የመጀመሪያውን የጣና ካፕ ውድድር ሊያካሂዱ ነው።

ዋናዎቹ የክለቦች ውድድሮች ከመጀመራቸው በፊት የቅድመ ውድድር ዝግጅቶች አካል የሆኑት የከተማ ዋንጫ ውድድሮች በሀገራችን እንደሚደረጉ ይታወቃል። በዋናነት የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በመዲናው ለዓመታት ሲደረግ የነበረ ሲሆን ከዓምና ጀምሮ ደግሞ የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ውድድር ሀዋሳ ላይ መከናወን ይዟል። አሁን ደግሞ ባህር ዳር ከተማ የጣና ካፕ በሚል ስያሜ ሊደረግ እንደሆነ ዛሬ አመሻሽ በተሰጠ መግለጫ ይፋ ሆኗል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እና ጎፈሬ በጋራ እንደሚያዘጋጁት የተገለፀውን ይህንን ውድድር አስመልክቶ ከአመሻሽ 11 ሰዓት ጀምሮ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ እና የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የባህልና ቱሪዚም ስፖርት መምሪያ ሀላፊ አቶ አብርሃም አሰፋን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል። በቅድሚያም የከተማው ከንቲባ ዶ/ር ድረስ እና የጎፈሬ ትጥቅ አምራች ተቋም ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን ስምምነቱን በፊርማቸው አፅንተዋል። በማስከተልም ስለ ውድድሩ ገለፃዎች መደረግ ጀምረው ክቡር ከንቲባው መድረኩን በቅድሚያ ተተክበዋል።

“ዛሬ በጎፈሬ እና በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር መካከል የመግባቢ ሰነድ ተፈርሟል። ስምምነቱም በከተማችን የጣና ካፕ የእግር ኳስ ውድድር ለማካሄድ ነው። ውድድሩን እንድናዘጋጅ ገፊ ምክንያት የሆነው በክልላችን ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበረው ነገር በኢኮኖሚው ላይ የፈጠረው ችግር ለማስተካከል እና ነገሮችን ወደ ነበረበበት ለመመለስ ነው። በዚህም በባህር ዳር የተለያዩ ሁነቶችን በማዘጋጀት ማኅበረሰቡ እና ተዳክሞ የነበረው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ ነው። በተለይ ከተማችን የቱሪስት መዳረሸሰ ስለሆነች ሴክተሩን ለማነቃቃት ስፖርታዊ ውድድሮች ወሳኝ በመሆናቸው ከውጪም ሆነ ከሀገር ውስጥ ፍላጎቱ ያላቸውን 8 ክለቦች ጋብዘን ውድድራችንን እናከናውናለን። በውድድሩ የተለያዩ ሽልማቶች ይኖራሉ። ክለቦችም ልምዶችን የሚቀያይሩበት ነው።” ካሉ በኋላ አቶ አብርሀም አስከትለው ተከታዩን ሀሳብ በስፍራው ለተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት አጋርተዋል።

“የጣና ካፕ ከመደበኛ የውድድር ወቅት በፊት የሚካሄድ ነው። ክለቦች በቅድመ ውድድር ዝግጅት ወቅት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን የሚያደርጉበት እና ያላቸውን አቅም የሚፈትሹበት ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ የአዲስ አበባ ከተማ እና የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ውድድሮች ተከናውነዋል። እኛ ደግሞ ካለን አቅም እና ፍላጎት የተነሳ በጣም የዘገየ ነው ብለን ብናስብም ዘንድሮ ለመጀመር አስበናል። ባህር ዳር የስፖርት፣ ቱሪዝም እና የትምህርት ከተማ ነች። በርካታ ምቹ ሁኔታዎች በከተማችን አሉ። በቅርቡ እንዳያችሁት የመጨረሻ የሊጉን ጨዋታ በተመሳሳይ ሰዓት በሦስት ስታዲየሞች አከናውነናል። ይህ በቂ የስፖርት መሰረተ ልማት እንዳለን ይጠቁማል። ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ክለቦች ለቅድመ ውድድር ዝግጅት ከተማችንን ይመርጧታል። ዝግጅታቸውን እኛ ጋር አድርገው የአቋም መለኪያ ጨዋታ የሚያደርጉት ግን ወደ ሌላ ከተማ ሄደው ነው። አሁን ግን እዛው ጨዋታዎችንም ያገኛሉ። በተረፈ ያለንበትንም ሁኔታ ለማስተካከል ነው። ለውድድሩ ጥሩ እቅድ አቅደን የሚመለከተውን የኮሚቴ አደረጃጀት አቋቁመን ነው ወደዚህ የውል ስምምነት የመጣነው። ስለዚህ በሜዳ፣ በጤና እና ሀብት አሰባሰብ ረገድ በደንብ እየተዘጋጀን ነው። በአጠቃላይ የተሻለ የውድድር ወቅት እንደሚኖረን ተስፋ እያደረግን ክለቦችን እንዲሳተፉ እንጋብዛለን።” ብለዋል።

ውድድሩ የሚካሄድበት ጊዜ የቀጣይ ዓመት ፕሪምየር ሊግ የሚጀመርበትን ቀን ታሳቢ በማድረግ እንደሚወጣ ተመላክቷል። እስካሁን ባለው መረጃም ሊጉ መስከረም 20 ስለሚጀመር የጣና ካፕ ከመስከረም የመጀመሪያ ቀናት እስከ አጋማሽ ድረስ እንደሚደረግ ተጠቁሟል። ምናልባት ውድድሩ ከተራዘመም ከመጀመሪያው ቀን ሦስት ሳምንት ቀድሞ አንድ ሳምንት ሲቀረው ደግሞ እንደሚፈፀም ተገልጿል።

ጎፈሬ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ ውድድሩን የሚያዘጋጅ ሲሆን ክለቦችን መጋበዝ እና ስፖንሰሮችን ማፈላለግ ላይ ከትጥቅ ሥራው ጎን ለጎን ስፖርታዊ ሁነቶችን ማዘጋጀቱ ላይ ልምድ ስላለው እንደሚያግዝ ተጠቁሟል። በውድድሩ በፕሪምየር ሊግ የሚሳተፉ ክለቦችን ጨምሮ በከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ እንዲሁም ከውጪ የሚመጡ ክለቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ በመግለጫው ተገልጿል። በመጨረሻም የከተማው ከንቲባ ውድድሩ በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት እንደሚያገኝ ተናግረዋል።