ሲዳማ ቡና የግብ ዘብ አስፈርሟል

በዝውውሩ በንቃት እየተሳተፈ የሚገኘው ሲዳማ ቡና ኢኳቶሪያል ጊኒያዊውን ግብ ጠባቂ ወደ ስብስቡ መቀላቀሉ ተረጋግጧል።

ጊዜያዊ አሠልጣኙ ወንድማገኝ ተሾመን ዋና አድርጎ የሾመው ሲዳማ ቡና የቀጣይ ዓመት ስብስቡን እያጠናከረ የሚገኝ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ኢኳቶሪያል ጊኒያዊውን ግብ ጠባቂ ፍሊፕ ኦቮኖን በአንድ ዓመት ውል ማስፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

1 ሜትር ከ83 ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው ኦቮኖ 2010 ላይ መቐለ 70 እንደርታን በመቀላቀል ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ሲሆን ሁለት ዓመታትን በክለቡ አሳልፎ 2011 ላይ የሊጉን ዋንጫም ከፍ ማድረግ ችሎ ነበር። ከኢትዮጵያ ከወጣ በኋላ ለሀገሩ ክለብ ፉቱሮ ኪንግስ ሲጫወት የነበረው ተጫዋቹ በቀጣይ ዓመት በሲዳማ ቤት ለመጫወት የቅድመ ስምምነት ፊርማውን ማኖሩ ታውቋል።