ወልቂጤ ከተማ ተጨማሪ ተጫዋች አስፈርሟል

ሰራተኞቹ ስምንተኛ ተጫዋች ወደ ስብስባቸው ሲቀላቅሉ የመስመር አጥቂያቸውንም ውል አድሰዋል።

በቀጣዩ የውድድር ዓመት በአሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚመሩት ወልቂጤ ከተማዎች ዘግየት ብለውም ቢሆን በዝውውር መስኮቱ ጥሩ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ። በዛሬው ዕለትም አንድ አዲስ አጥቂ አስፈርመው የአንድ ነባር ተጫዋቻቸውን ውል አድሰዋል።

ቡድኑን የተቀላቀለው ተጫዋች የኋላሸት ሰለሞን ነው። በዲላ ከተማ መነሻውን ያደረገው ይህ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ወደ ኢኮስኮ እና ደቡብ ፖሊስ አቅንቶ የተጫወተ ሲሆን ዓምና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዳግም ሲመሰረት ተቀላቅሎ በከፍተኛ ሊጉ ሲጫወት ነበር። አሁን ደግሞ ከቀድሞ አሠልጣኙ ገብረክርስዮስ ቢራራ ጋር ለመስራት ወልቂጤን ተቀላቅሏል።

በተያያዘ ዜና ቡድኑ የመስመር አጥቂው አብዱልከሪም ሳኒን ውል ለተጨማሪ የውድድር ዓመት ማራዘሙን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።