አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ያላቸውን ውል በተመለከተ ሀሳብ ሰጥተዋል

👉”ውሉ አልቋል። የምትስማማ ከሆነ ትቀጥላለህ ፤ ካልሆነ ሌሎች አማራጮችን ታያለህ”

👉”በእኔ በኩል ከክለብ የመጡ የተጨበጡ ጥያቄዎችን ከብሔራዊ ቡድኑ መልስ ሳላገኝ አልመልስም ብዬ የዘለልኳቸው ሁለት ሦስት ጥያቄዎች አሉ”

👉”አሁን ላይ የተጨበጠው መረጃ የሥራ አስፈፃሚው ለመጨረሻ ጊዜ እንዳልተሰበሰበና ጉዳዩን ለመመልከት ፍቃደኛ ቢሆኑም እንዳልተገናኙ ነው”

👉”…እነሱም ከእኔ የተሻለ አማራጫቸውን ሊያዩ ይችላሉ ፤ እኔም ሀገሬን ማገልገል እየፈለኩ እስካሁን ያጣሁት ነገር ቢኖርም ከዚህ በኋላ እነርሱን እየጠበኩ መቀመጥ አለብኝ ብዬ አላስብም”

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የቻን ማጣሪያ ደቡብ ሱዳንን የገጠሙበትን የደርሶ መልስ ጨዋታ አስመልክቶ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን ከቆይታ በኋላም የመግለጫውን ሙሉ ይዘት ይዘን የምንቀርብ ይሆናል። አስቀድመን ግን አሠልጣኙ ከውላቸው ጋር ተያይዞ ያነሱትን ሀሳብ እንደሚከተለው አቅርበናል።

“ከፌዴሬሽኑ ጋር የተጀመሩ ነገሮች አሉ። እርግጥ ጠንከር ያለ ንግግር አላደረግንም። በእኔ በኩል መሆን ያለባቸውን ነገሮች አቅርቤያለው። ከዚህ በኋላ ለእኔም ሆነ ለብሔራዊ ቡድኑ የመጨረሻ ሰዓት ስለሆነ ብዙ የሚያሳስብ አይመስለኝም። እኔ ይሄ ብዙ አያሳስበኝም። ውሉ አልቋል። የምትስማማ ከሆነ ትቀጥላለህ ፤ ካልሆነ ሌሎች አማራጮችን ታያለህ። በእኔ በኩል ከክለብ የመጡ የተጨበጡ ጥያቄዎችን ከብሔራዊ ቡድኑ መልስ ሳላገኝ አልመልስም ብዬ የዘለልኳቸው ሁለት ሦስት ጥያቄዎች አሉ። በእግር ኳስ ቅጥርም ስንብትም ቅርብ ስለሆነ ከጨዋታው በላይ አያሳስበኝም። የሩዋንዳ ጨዋታ ከፊት አለ። ማሰብም መዘጋጀትም የምፈልገው ለዛ ነው። በግሌ ራሴ ነፃ እንደሆንኩ ነው የሚሰማኝ። ምክንያቱም ቀድመው መተው የነበሩትን ነገሮች ፌዴሬሽኑን ሳላናግር ውሳኔ ውስጥ ላለመግባት አሳልፌያቸዋለው። ይሄንን ደግሞ ፌዴሬሽኑም ያውቃል። ከዚህ በኋላ ሁለተኛ ጥበቃ በእኔ በኩል መኖር አለበት ብዬ አላስብም። ለጊዜው ግን ከሌላ ቦታ የመጣ ነገር ስለሌለ ውሌን ከመጨረስ ውጪ ብዙ የሚያሳስብ ነገር የለም። ከሩዋንዳ ጨዋታ ጋር ግን አይገናኝም። ውል እስካለ ድረስ ስራዎችን በትኩረት መስራት ነው። ልክ የደቡብ ሱዳኑን ጨዋታ እንዳጠናቀቅን ማሰብ የጀመርነው ስለ ሩዋንዳው ፍልሚያ ነው።

“በእኔ በኩል ስለቀጣዩ እቅዳቸው ጠይቄ ፍቃደኛ እንደሆኑ ነግረውኝ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ብቀጥል የቡድኑ ስታንዳርድ ምን መሆን አለበት የሚለውን ከተጫዋቾች፣ ከአሠልጣኞች ስታፍ እና ከራሴ አንፃር በፅሁፍ ለሥራ-አስፈፃሚው አቅርብ ተብዬ አቅርቤያለው። ወደ ታንዛኒያ ከመሄዴ በፊት ሥራ አስፈፃሚው ጉዳዩን እንዳየና ዝርዝሮቹን ስመለስ ልናወራ እንደምንችል ነው የተነገረኝ። አሁን ላይ የተጨበጠው መረጃ የሥራ አስፈፃሚው ለመጨረሻ ጊዜ እንዳልተሰበሰበና ጉዳዩን ለመመልከት ፍቃደኛ ቢሆኑም እንዳልተገናኙ ነው። ይሄ ማለት አሁን የተጨበጠ ነገር የለም ማለት ነው። በግልፅ የገባኝ ነገር ፍላጎቱ አላቸው ግን ከወቅቱ አንፃር ቁጭ ብለው ዝርዝር ነገሮችን አይተውታል ብዬ አላስብም። ስለዚህ ይህ ከሆነ እነሱም ከእኔ የተሻለ አማራጫቸውን ሊያዩ ይችላሉ ፤ እኔም ሀገሬን ማገልገል ብፈልግም እስካሁን ያጣሁት ነገር ቢኖርም ከዚህ በኋላ እነርሱን እየጠበኩ መቀመጥ አለብኝ ብዬ አላስብም። ባለሙያ ነኝ። ሲፈክጉህ እና ስትፈልግ ትቆያለህ። መፈለግህን አሳይተህ እነሱ ውሳኔ ላይ ካልደረሱ ህይወት፣ ቤተሰብ እና ስራ አለ። ይህ ሙያ ነው። ተነጥለህ መቀመጥ የለብህም።”