አሠልጣኝ ውበቱ አባተ መግለጫ ሰጥተዋል

👉”ከመጀመሪያው ጨዋታ አንፃር የሁለተኛው ጨዋታ በሁሉም የጨዋታ ክፍሎች ላይ መሻሻል የታየበት ነበር”

👉”እኛ ራሳችንን የምስራቅ አፍሪካ የተለየ ቡድን አድርገን ነው የምናስበው ፤ ግን አይደለንም”

👉”…በሌሎች ባልተመረጡ ተጫዋቾች እና አሁን በቡድኑ ውስጥ ባሉ ተጫዋቾች መካከል ሰፊ ልዩነት አለ ማለቴ አይደለም”

👉”በዚህ የእፎይታ ጊዜ መንግስት አስቦበት የሜዳ ጥያቄዎቻችንን የምንመልስ ከሆነ በሜዳችን የሚገኘውን ጥቅም በመጠቀም ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለመግባት ሰፊ ዕድል እናገኛለን”

በቻን ማጣሪያ የኢትዮጰያ ብሔራዊ ቡድን ከደቡብ ሱዳን ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታውን ታንዛኒያ ላይ አከናውኖ በድምር ውጤት 5ለ0 አሸንፎ ወደ ሀገሩ መመለሱ ይታወቃል። ቡድኑ ባሳለፍነው ዓርብ ወደ ሀገር ቤት ቢመለስም በዛሬው ዕለት ጨዋታዎቹን አስመልክቶ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከብዙሃን መገናኛ አባላት ጋር ተገናኝተው ሀሳባቸውን አጋርተዋል። በመግለጫው የተነሳውን የአሠልጣኙን ኮንትራት በተመለከተ የተሰጠውን አስተያየት ከደቂቃዎች በፊት አስነብበን የነበረ ሲሆን ሌላውን የመግለጫውን ክፍል ደግሞ አሁን የምናቀርብ ይሆናል። በቅድሚያም አሠልጣኝ ውበቱ ተከታዩን ሀሳብ ሲያጋሩ ተደምጠዋል።

“ሁላችሁም እንደተከታተላችሁት ሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታን ታንዛኒያ ላይ ከደቡብ ሱዳን ጋር አድርገናል። በመጀመሪያው ጨዋታ ተጋጣሚያችን ጠንካራ የሆነ መከላከል፣ የአንድ ለአንድ ጨዋታዎች እና ክፍተቶችን ያለመስጠት እንዲሁም ሀይል የተቀላቀለበት ጨዋታ መርጠው የቀረቡበት ነበር። ይሄንን ሰብሮ የተሻሉ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ላይ እኛ ክፍተቶች ነበሩብን ፤ ይህንን ተከትሎ ጨዋታውን ያለ ግን 0ለ0 ነበር ያጠናቀቅነው። ከቀናት በኋላ ግን በመጀመሪያው ጨዋታ ያየነውን ክፍተት ታሳቢ በማድረግ ለመዘጋጀት ሙከራ አድርገናል። እነሱ በሁለተኛውም ጨዋታ በተመሳሳይ አቀራረብ አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ለመምጣት እና ጫና ለመፍጠት ከመሞከር ውጪ ብዙ የከበደን ነገር አልነበራቸውም። የመጀመሪያው ጎል እስከሚቆጠር ድረስ ጠጣር ነበሩ። ከዛ በኋላ ግን በተሻለ ጨዋታውን መቆጣጠር እና ግቦችን ማስቆጠር ለእኛ ቡድን ከባድ አልነበረም። ይህንንም ተከትሎ በሰፊ ብልጫ 5ለ0 ማሸነፍ ችለን ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈናል። ከመጀመሪያው ጨዋታ አንፃር የሁለተኛው ጨዋታ በሁሉም የጨዋታ ክፍሎች ላይ መሻሻል የታየበት ነበር። ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣትም የነበረን ቁርጠኝነት የተሻለ ነበር። በቀጣይ ከሩዋንዳ ጋር የምንጫወት ይሆናል። ለዚህም ጨዋታ ትኩረታችንን ሰጥተን ዝግጅታችንን እንጀምራለን።” በማለት ንግግራቸውን ካሰሙ በኋላ በስፍራው ከተገኙ ጋዜጠኞች የቀረበላቸውን ጥያቄ መመለስ ይዘዋል።

የመጀመሪያው ጨዋታ ላይ ተጫዋቾቹ ላይ ስለታየው ክፍተት…?

“አንደኛ ተጫዋቾቹ አጭር የእረፍት ጊዜ ነው የነበራቸው። ሁለተኛ ደግሞ የተጫዋቾች የዝውውር ወቅት ስለነበር ቀጣይ ማረፊያቸውን ለማወቅ ትንሽ የተጨናነቀ ሳምንት ነበር ሲያሳልፉ የነበረው። ተጫዋቾቹ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ግንኙነት ፈጥረው ውሳኔ ለማግኘት ሲሄዱ ነበር። ይህ አድካሚ ነገር ነበረው። በአምሮም ሆነ በአካል የዛሉበት ሁኔታ እና ሙሉ ለሙሉ ትኩረት መስጠት የቻሉበት ሁኔታ እንዳልነበር ቀደም ብዬ ገልጬ ነበር። ይሄ ጨዋታው ላይ ተፅዕኖ አልፈጠረም ማለት አይቻልም። በተወሰነ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል።

“ሌላው የመጀመሪያውን ጨዋታ ከባድ የሚያደርገው ነገር ስለ ደቡብ ሱዳን መረጃዎች ማግኘት ቢቻልም ቻን ላይ የሚመጣውን የደቡብ ሱዳን ቡድን ማወቅ አለመቻል ነው። ይሄ ከባድ ነው። የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ቡድን ከሌሎች ቡድኖች ጋር ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ማየት ይቻላል ፤ ግን ለቻን የሚዘጋጀው ቡድን እነዛን ያካተተ ስላልሆነ የቡድኑን አቋም ሙሉ ለሙሉ ማወቅ አይቻልም። ይሄ አስቸጋሪ ነገር ነበር። ሜዳ ላይ በመጀመሪያው ጨዋታ ካየናቸው በኋላ ግን በምን አይነት መንገድ መቅረብ እንደምንችል መነሻ ነገር ሰጥቶናል። የመጀመሪያው ጨዋታም ከሁለተኛው ከባድ የነበረበት ምክንያት ይሄ ነው።

“ሁለተኛው ነገር የመጨረሻው የማጥቂያ ክልል ላይ ስንደርስ የመጣደፍ እና የመቻኮል ነገር ነበር። የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ሰዓቶችን ጠብቆ ለተገኘው ሰው መስጠት እና ሁኔታውን መጨረስ ላይ ክፍተቶች ነበሩ። በሁለተኛውም ጨዋታ እርሱን የማረም ስራ ነው የሰራነው። ከመጀመሪያውም እንዲቀለን ያደረገው ይሄ ነው።”

የተጋጣሚያችሁ ደቡብ ሱዳን ደካማ ጎን…?

“ደቡብ ሱዳን ጠንካራ ቡድን ነው። አምስት ጎል ማግባታችን አንድ ነገር ቢሆንም ጥሩ መስመር ላይ እንዳሉ ነው ያየውት። 90 ደቂቃ ተሯሩጦ የሚጫወት ቡድን አላቸው። ታክቲካሊም ዲሲፕሊምድ ናቸው። ስለዚህ ያን ያህል ቀላል ቡድን ነው ብዬ መናገር ይቸግረኛል።”

በቻን ውድድር ወጣት ተጫዋቾችን ስለመጠቀም…?

“እንደ ሌሎች ብሔራዊ ቡድኖች ወጣቶችን ለምን አናሳትፍም የሚለው ጥያቄ ሌሎች ስላላቸው ነው የሚጠቀሙት። ሌሎች ብሔራዊ ቡድኖች ተጫዋቾቻቸው አውሮፓ ወይም ጎረቤት ሀገር ነው የሚጫወቱት። ስለዚህ በዚህ ውድድር ማጫወት አይችሉም። እኛ የሌለንን አምጥተን በአፍሪካ ዋንጫ ማሳተፍ እንደማንችለው ሁሉ እነሱም ይሄንን ማድረግ አይችሉም። ስለዚህ ሀገር ውስጥ ያሉትን ተጫዋቾች መጠቀሙ ብዙ ችግር የለውም። ውድድሩ ላይ ሁለት ጊዜ ያበቁንን ባለሙያዎች ማክበር እንዳለብን አምናለው ፤ እኔም ማክበሩ አለኝ። ግን አሉን የምንላቸውን ተጫዋቾች ይዘን ቀርበን ምን አድርገናል? እኛ ራሳችንን የምስራቅ አፍሪካ የተለየ ቡድን አድርገን ነው የምናስበው። ግን አይደለንም። ይሄ እንዳልሆነ ደግሞ በተግባር ያየነው ነው። በዋናውም ሆነ በዚህ ውድድር ያለን ታሪክ ያን ያህል የሚያኩራራ አይደለም። ስለዚህ በሁለተኛ ቡድናችን እንጫወት የሚያስብል ደረጃ የሚያስደርስ አይደለም። ይሄንን ስል በሌሎች ባልተነመጡ ተጫዋቾች እና አሁን በቡድኑ ውስጥ ባሉ ተጫዋቾች መካከል ሰፊ ልዩነት አለ ማለቴ አይደለም። የትኛውም ተጫዋች በማንኛውም ጊዜ በሌላ ተጫዋች ሊተካ እንደሚችል አምናለው። ግን እነዚህን ለአፍሪካ ዋንጫ ፤ እነዚህን ደግሞ ለቻን ብለን የምናስብበት ብሔራዊ ቡድን አለን ብዬ አላስብም። ሀገራችን በአፍሪካ ደረጃ ያላት ደረጃ እዛ ላይ ነው ብሎ መናገር የሚያስደፍር አይመስለኝም። ከ7 ጊዜ ሁለቴ ተካፍለናል ግን ሁለቱንም ከምድባችን ማለፍ አልቻልንም። አንደኛውን እንደውም ያለምንም ጎል ነው የመጣነው። እንደውም እዚ ውድድር ላይ ከተካፈልን ቆይተናል። ከቻልን ሩዋንዳን አሸንፈን ወደ ቻን ለመግባት መዘጋጀት እና ውድድሩ ላይ ደግሞ አሁን ያሉትን ተጫዋቾች ሀገራቸውን እንዲያስተዋውቁ ማድረግ ነው። እኛም እየሰራን ያለነው ለዚህ ነው። ይሄንን ስል ግን ላልተመረጡ ተጫዋቾች ያነሰ ግምት ኖሮኝ አይደለም። ማንኛውም ተጫዋች ቦታውን እስከመጠነ ድረስ ወደዚህ መጥቶ መጫወት እንደሚችል አምናለው። ለራሳችን የምንሰጠው ግምት ግን ትንሽ የተጋነነ ይመስለኛል።”

የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ስለመራዘሙ…?

“መራዘሙ ሀገርን ይጠቅማል። እኔ ልኖርም ላልኖርም እችላለው። ይሄ ቡድን በጣም ጥቂት ጨዋታዎችን ነው በሜዳው የተጫወተው። በጣም በርካታ ጨዋታዎችን ከሜዳው ውጪ ነው ያደረገው። ስለዚህ በዚህ የእፎይታ ጊዜ መንግስት አስቦበት የሜዳ ጥያቄዎቻችንን የምንመልስ ከሆነ በሜዳችን የሚገኘውን ጥቅም በመጠቀም ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለመግባት ሰፊ ዕድል እናገኛለን። ስለዚህ አሠልጣኙ ማንም ሊሆን ይችላል። ሀገር ግን ትጠቀማለች ፤ በሜዳ መጫወት ብዙ ጥቅም ስላለው። ከምንም በላይ የስነ-ልቦና ጥቅም ስላለው ህዝብ የራሱን ቡድን ሜዳው ላይ ሲጫወት ማየት ስላለበት ጥቅም አለው። ሰው በቴሌቪዥን ቁጭ ብሎ ቡድኑን ማየት ይችላል ግን ለሊት ተነስቶ ተጋፍቶ ትኬት ቆርጦ ሜዳ ገብቶ የራሱ የሆነውን ቡድን ይመለከታል። ይህ ትልቅ ኩራት ነው። ስለዚህ መራዘሙ ትልቅ ጥቅም ነው ብዬ አስባለው።”