ለፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት አቶ መላኩ ፈንታ መግለጫ ሰጥተዋል

👉”ልንመረጥ ይገባል ብለን የምናስበው በሀሳባችን ነው እንጂ በገንዘባችን አይደለም ፤ በሀሳባችን እንጂ በኔትወርካችን አይደለም ፤ በሀሳባችን እንጂ ከመጣንበት ዝርያ አይደለም።”

👉”የምርጫ መሪ ቃላችን ለለውጥ! ለመለ ‘ወጥና ለመለወጥ! የሚል ነው”

👉”የኢትዮጵያ ምርጫዎች ለአላማ እና ለለውጥ ሳይሆን የተፈለገን ሰው ለማምጣት የሚደረጉ እንደሆነ ሁላችሁም የምታውቁት ነው”

👉”ኢ-ፍትሃዊ ነገሮች ከሌሉ ይዘነው በመጣነው ሀሳብ እናሸንፋለን ብለን እናስባለን”

👉”ራሴን አላገልም! አሁንም ቃሌን ደግሜ እሰጣለሁ ከምርጫው ራሴን አላገልም”

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንታዊ እና የሥራ-አስፈፃሚ ምርጫ በሳምንቱ መጨረሻ እንደሚከናወን ይጠበቃል። የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴውም 3 ለፕሬዝዳንትነት 32 ለሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት እጩ የሆኑ ግለሰቦችን ከቀናት በፊት ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። በፕሬዝዳንትነት ከሚወዳደሩት ግለሰቦች መካከል አንዱ የአማራ ክልል ተወካይ የሆኑት አቶ መላኩ ፈንታ ደግሞ ዛሬ በሂልተን ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ለ100 ደቂቃዎች የተጠጋውን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት አቶ መላኩ ፈንታ ሀሳባቸውን በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ከፍለው አቅርበዋል። በዚህም ጋዜጣዊ መግለጫውን መስጠት ስላስፈለገበት ምክንያት፣ ምርጫውን በተመለከተ ያላቸውን ሀሳብ፣ በፕሬዝዳንትነት ቢመረጡ ምን ሊከውኑ እንዳሰቡ እና ሀሳባቸውን ለማሳካት ስላላቸው ዝግጁነት ገለፃ አድርገዋል። በቅድሚያም ጋዜጣዊ መግለጫውን ለመስጠት ለምን አስፈለገ በሚለው ላይ ተከታዩን ሀሳብ በስፍራው ለተገኙ በርካታ የብዙሃን መገናኛ አባላት አጋርተዋል።

“ሀገራችን በእግርኳስ ያለችበት ሁኔታ ይታወቃል። ካለበት ደረጃም ውጤታማ እና ወደ ከፍታ እንዲሄድ ያስፈልጋል። ይሄ እንዲሆን ደግሞ ምርጫው ፍታሀዊ መሆን አለበት። ይህንንም ነገር እኔም ተመርጬ ስራውን ለማከናወን አስባለው። እኔ በግሌ የእግርኳስ ምርጫ ምን ይፈልጋል የሚለውን ለማጣራት ሞክሬያለው። በምገባበት ጉዳይም በእውቅና ለመግባት ሥሰራ ቆይቻለው። ከዚህ በመነሳት ዶክመንቶችን ለማየት ሞክሬያለው። ከሚዲያው፣ አሠልጣኞች፣ ዳኞች፣ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ጋር ኳሳችን ምን ይፈልጋል የሚለውን በተመለከተ ስወያይ ቆይቻለው። በዚህም ምን ሊሰራ እንደሚገባ አውቄያለው። ያገኘኋቸውም መደምደሚያዎች አሉ። አንደኛው ስለምርጫው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ምን ሊሰራ ይገባል የሚለውን ጉዳይን የተመለከተ ነው። መግለጫውም በምርጫው ሂደት እና በምሰራቸው ስራዎች ላይ ያለውን ሀሳብ እንዳሳውቅ በማሰብ ነው የተዘጋጀው።” ካሉ በኋላ የምርጫውን ሂደት በተመለከተ ደግሞ ሀሳባቸውን አስከትለዋል።

“ምርጫን በተመለከተ ዋናው ነጥብ ምርጫው ፍታሀዊ እንዲሆን ነው። ይህ ልምድም መሆን አለበት። ሰዎች በሜሪታቸው መምጣት አለባቸው። ምርጫው ከተበላሸ የእግርኳሳችንም ውጤት የተበላሸ ነው የሚሆነው። ቅድም ባልኩት መልኩ ቀደምት ምርጫዎችን ለማጥናት ሞክሬያለው። የኢትዮጵያ ምርጫዎች ለአላማ እና ለለውጥ ሳይሆን የተፈለገን ሰው ለማምጠጣት የሚደረጉ እንደሆነ ሁላችሁም የምታውቁት ነው። ብዙ ጊዜ የምርጫ መወዳደሪያ ሀሳብ አይቀርቡበትም። ቃል የተገቡ ሀሳቦችም አይተገበሩም። ለማስመረጥ የሚኬድበት መንገድም በአብዛኛው ጤናማ ሂደት የለውም። በገንዘብ እና በኔትወርክ ለማስመረጥ የሚደረገው ጥረት በጣም ትልቅ ነው። ሚዲያውም ቢሆን ለወገነው አካል የሚቆረቆርበት ፤ ፖለቲካም ተፅዕኖ የሚያደርግበት ነው። ምናልባት አንዳንድ እጩዎችም ራሳቸውን እንዲያገሉ የሚደረግበት ነገር እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው። የምርጫ ሂደቱንም ለማዛባት የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ነው። በገንዘብም ድምፅን ለማስቀየር የሚደረግ ጥረት አለ። የአንዱን ድምፅ ወደ አንዱ ለማስተላለፍ የሚደረጉ ጥረቶችም አሉ። ምናልባትም መራጮች የመረጡበትን ትኬት ፎቶ አንስተው ለመረጡት ሰው ሲያሳዩ ብቻ ገንዘባቸውን የሚቀበሉበት ነገር እንዳለ የአደባባይ ሚስጥር ነው። በዚህ ሂደት የምናደርገው ምርጫ ተዓማኒነት ብቻ ሳይሆን የግጭት እና የትርምስ መነሻ ነው። ወደ ፊፋ እና ካፍ የሚሄዱ ጉዳዮችም በርካታ እንደሆኑ ሁላችሁም ታውቃላችሁ። ይሄ ሂደት ለሀገር እና ለእግርኳሱ አይጠቅምም። ስለዚህ ይበቃል ማለት ይጠቅማል የሚል እምነት አለኝ።

“በእኛ በኩል ምርጫው ፍትሀዊ እንዲሆን እንፈልጋለን። የክልልላችን አመራሮችም ብቁ ተወዳዳሪ ማቅረብ አለብን ብለን ተወያይተንበት ለሀገር የሚጠቅም ተወዳዳሪ አቅርበናል። ልንመረጥ ይገባል ብለን የምናስበው በሀሳባችን ነው እንጂ በገንዘባችን አይደለም ፤ በሀሳባችን እንጂ በኔትወርካችን አይደለም ፤ በሀሳባችን እንጂ ከመጣንበት ዝርያ አይደለም። እኛ የለውጥ ሀሳብ ነው ይዘን የምንቀርበው። ይሄንን ማኅበረሰቡ ሊያውቅ ይገባል።ይህንን ተከትሎ ምርጫው ፍትሀዊ እንዲሆን እንጥራለን። ህገወጥነቶች ካሉ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈቱ እናደርጋለን ፤ ከዛ ካለፈ ግን ወደ ህግ እንወስደዋለን። ይሄ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይም መለመድ አለበት ብለን ስለምናስብ። ውጤቱ ምንም ይሁን ምንም የምርጫ ሂደት ፍትሀዊ እንዲሆን መስራት የሁላችንም ተግባር መሆን አለበት ብለን እናስባለን።”

በከፍተኛ ሀገራዊ የሥራ ኃላፊነቶች፣ በሥራ አመራር ቦርድ መሪነትና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በመሳተፍ በርካታ ስኬቶችን እና ተጠቃሽ ውጤቶችን እንዳስመዘገቡ እንዲሁም አሻራቸውን ባሳረፉባቸው ተቋማት ሁሉ አዳዲስ የለውጥና የማሻሻያ ሀሳቦችን አመንጭቶ በመተግበት በስፋት እንደሚታወቁ የሚናገሩት አቶ መላኩ አስከትለው መሪ ቃላቸውን ይፋ በማድረግ ገላፃቸውን ቀጥለዋል።

“የምርጫ መሪ ቃላችን ለመለ ‘ወጥና ለመለወጥ! የሚል ነው። በመጀመሪያ ራስን መለወጥ ያስፈልጋል ፤ ኳሳችን ትንሳዔ ያስፈልገዋል ነው። ይሄንን አምኖ መጀመሪያ ሰው መለወጥ ያስፈልገዋል። ከዛ ሌላውን ለመለወጥ መስራት አለበት። ለዚህም ዝግጁ ነን። በዚህም የምርጫ መሪ ቃላችንን እና የምንሰራቸውን እቅዶች አዘጋጅተን እየተንቀሳቀስን ነው። ከዚህ ምርጫ ምን ይጠበቃል የሚለው ዓላማን መዓከል ያደረገ ምርጫ እንዲኖር ማድረግ ፤ ኢ-ፍትሃዊ ነገሮች ከሌሉ ይዘነው በመጣነው ሀሳብ እናሸንፋለን ብለን እናስባለን። ግን ለማሸነፍ ባዶ እጃችንን አንገባም።”

ዘለግ ያለ ማብራሪያቸውን የቀጠሉት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንትነት እጩ ተወዳዳሪ አቶ መላኩ ከተመረጡ በኋላ ሊሰሯቸው ስላሰቧቸው ነገሮች ደግሞ ሀሳብ ማጋራት ይዘዋል።

“ልሰራ ያሰብኳቸውን ነገሮች መነሻ ያደረጉት ቅድም በጠቀስኩት መጠነኛ ጥናት ነው። አንደኛው የለውጥ መነሻ ሀሳቡ ስፖርት እና እግርኳሱን መዓከል ያደረገ ነው። እግርኳስ ከስፖርታዊ ባህሪው በዘለለ ማርኬታዊ እንዲሁም ኢ-ማርኬራዊ ባህሪያት አሉት። ስለዚህ ስለእግርኳሱ ስናስብ ውጤት እና እድገቱን ብቻ ሳይሆን ከጎኑ ያሉትን የገበያ ባህሪያ እና ቢዝነስ ነክ ያልሆኑ ነገሮችን ጠንቅቆ ማወቅ እና ሁለቱንም እኩል አድርጎ ማስኬድ ያስፈልጋል። እግርኳሱ በዓለም ደረጃ ትልቅ ማርኬት እየሆነ እና እያደገ ነው ፤ ከስፖርት ሳይንስም ሆነ ከቢዝነስ አንፃር ማለት ነው።

“እኛ ካፍን መስርተናል ፤ ግን ከእኛ ጋር መስራቾቹ የት እንዳሉ ይታወቃል። ከእኛ ጋር በአፍሪካ ደረጃ መስራቾች የሆኑት አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስንት ተጫዋቾች እንዳላቸው ይታወቃል። እኛ ግን? ከዚህ ውጪ በአህጉራችን ብዙ ሀገራት ምርጥ አካዳሚዎች አሏቸው። አካዳሚዎች የሰለጠነ የሰው ሀይል ማምረቻ ብቻ ሳይሆን የገቢ ማስገኛ ዘዴዎችም እየሆኑ ነው። በተለይ በምዕራብ አፍሪካ ያሉ ሀገራት በዚህ ረገድ ጥሩዎች ናቸው። ክለቦቹም የራሳቸውን ገቢ ማስገኛ መንገዶች አሏቸው። ቅርባችን ሱዳን ውስጥ ራሱ 5 ስታር ሆቴል ያለው ክለብ አለ። ስለዚህ ብራንዲንግ ላይ በደንብ መሰራት ያስፈልጋል። ወደ እኛ ስንመጣ የት ነው ያለነው? የለውጡ ሀሳብም ከዚህ ይመነጫል።

“አንዱ ነገር ህዝባችን ትልቁ ሀብት ነው። በሀገራችን ያለው የህዝብ ብዛት ይታወቃል። አብዛኛው ደግሞ ወጣት እና ታዳጊ ነው። ስለዚህ ይህንን መጠቀም ያስፈልጋል። እነህንድ ከእኛ በህዝብ ብዛት ቢበልጡም እኛ ሀገር የእግርኳስ ታለንት በጣም አለ። ስለዚህ ታለንት ፈልገን ብናወጣ ትልቅ ነገር ነው። ህዝቡም እግርኳስ ይወዳል። ቀደምት ታሪካችንም በአፍሪካ ትልቅ ደረጃ ነበረን። ይሄንን ታሪካችንን እንደመንደርደሪያ ልንጠቀምበት እንችላለን። የተሰሩ ስራዎች እንደተጠበቁ ሆነው ውጤት አልባ ነን። በብሔራዊ ቡድን ደረጃም ሆነ በክለቦች ደረጃ በአህጉራዊ ደረጃ ያለን ውጤት ጅምር ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው ውጤት አልባ ነን። በአለም አቀፍ እና አህጉራዊ ተቋማት ያለን ተቀባይነት፣ ውከላ እና ደረጃም ብዙም አይደለም።” ካሉ በኋላ በእቅዳቸው መሰረት ለችግሮቹ ለመስጠት ያሰቧቸውን መፍትሔዎች አስቀምጠዋል። በዚህም አንደኛው ነገር ስፖርቱን ህዝባዊ ማድረግ፣ መሰረተ ልማቶችን ማሳደግ፣ በቢዝነስ ረገድ ክለቦች እና ፌዴሬሽኖች አስተማማኝ ገቢ እንዲያገኙ ማድረግ እና ውድድሮች በተገቢው መንገድ እንዲመራ ማድረግ እንዲሁም ለሴቶች ትኩረት ሰጥቶ መስራት ተገቢ እንደሆነ ዘርዝረዋል። አቶ መላኩ አክለውም ሥራዎችን የሚመለከታቸው ባለሙያዎች እና ባለእውቀቶች እንዲሰሩት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ለበርካታ አመታት ሲንከባለል ነበረ ያሉትን መዋቅራዊ እና መሰረታዊ ችግርም ለመለወጥ እና ለመለወጥ ዝግጁ ሆነው እንደመጡ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

በትምህርት ዝግጅታቸው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን እና ዓለም አቀፍ የገቢ አስተዳደር እንዲሁም በድህረ ምርቃ ዲፕሎማም በከተማ አስተዳደር እና ፕላንና ፋይናንስ ያገኙት አቶ መላኩ ዋና ዓላማቸው “ተቋማዊ አቅሙ የዳበረ፣ በኢትዮጵያውያን ሁሉን ቅቡል የሆነና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነቱ ከፍ ያለ” የእግርኳስ ፌዴሬሽን መገንባት እንደሆነ ተናግረዋል። ከለውጥ አስተሳሰቡ ጋር ተያይዞም “የለውጡ ምሶሶዎች” ሆነው ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር የሚሰሩት ሚዲያ፣ የግል ዘርፍ፣ ሕዝብ/ደጋፊ፣ ክለቦች፣ የክልል ፌዴሬሽኖች፣ ዓለም አቀፍዊ/አህጉራዊ ፌዴሬሽኖች እና መንግስት እንደሆነ ጠቆም አድርገው ግቦች እና የስትራቴጂ እርምጃዎችን አስረድተዋል።

“በአጫጭር ድሎች መርካት ሳይሆን ሥር-ነቀል ለውጥ መርሃችን ነው።” ካሉ በኋላም ተከታዮቹን ሰባት የግብ ነጥቦች አስቀምጠዋል።

1 መሰረታዊ ለውጥ በማካሄድ የተቋሙን የመፈፀም አቅም ማሳደግ – መሰረታዊ የለውጥ ጥናት በማካሄድ አደረጃጀትና የአሰራር ማሻሻያዎችን በመቅረፅ፣ በመተግበርና በቴክኖሎጂ ግብዓት በማዘመን፣ ባለሙያ በማደራጀትና በማሳተፍ ተቋሙን ሪብራንድ ማድረግ

2 የፌዴሬሽኑን አባላትና ክለቦችን በፋይናንስ ማጠናከር – ለእግርኳሱ ቀጣይነት ያለው እድገት ዘላቂነት ያለውና አስተማማኝ የገቢ ምንጭ ለመፍጠር በጥናት ላይ የተመሠረተና ወጤታማነታቸው በተረጋገጡ ዓለም አቀፍ ልምዶች ተቃኝቶ የስፖርቱን ማኅበረሰብና የግሉን ዘርፍ የሚያሳትፍ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት በመተግበር እግርኳሱ በቢዝነስ መርህ እንዲመራ ማድረግ

3 የእግር ኳስ መሠረተ ልማት እና ስፖርቱ በመላ ኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ማድረግ – ያለንን ሕዝብ ብዛት የሚመጥኑ፣ ከእግርኳስ ታሪካችንና ወዳድነታችን ጋር የሚመጣጠኑ፤ በዓለም አቀፍ መለኪያዎችም ምቹና ብቁ የሆኑ ስታዲየሞችንና የእግር ኳስ መሠረተ ልማትን በማስፋፋት በሌሎች ሀገራት ስታዲየሞች ለመጫወት የተገደደንበትን የማይመጥነንን ታሪክ ለዘለቄታው መቀየር ፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞም እግር ኳስ ሕዝባዊ መሰረቱ ተጠናክሮ በመላዋ ሀገሪቱ እንዲሰፋ የተተኪ ፕሮጀክቶችን አቅም መገንባት

4 ከስፖርት ቤተሰቡ ጋር በትብብር መስራት – ከእግር ኳሱና በአጠቃላይም ከስፖርቱ ቤተሰብና ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እና በቅንጅት በመሥራት ለስፖርቱ መጎልበት የሚረዱ የጋራ ራዕይ ሰንቆ ለተግባራዊነቱ መትጋት፤ ሚዲያውም ለስፖርቱ እድገት ገንቢ አስተዋፅኦውን አጠናክሮ እንዲቀጥል አጋርነትን ማጠናከር እና በውጤት የተመሰረተ የዕውቅና ሥርዓት በመዘርጋት ተግባራዊ ማድረግ

5 የብቁ ተወዳዳሪነትን አቅም መገንባትና
ማረጋገጥ – ውድድሮች በስፖርታዊ ጨዋነት ተከናውነው የመልካም ግንኙነት መድረክ እንዲሆኑና ለብልሹ አሰራር ተጋላጭ እንዳይሆኑ የሚያግዙ የአሰራር ማሻሻያዎችን በመተግበርና የሕግ ማዕቀፎችን በመቅረጽ፣ በሀገር ውስጥና በውጪ ተፎካካሪ የሆኑ ብሔራዊ ቡድኖች፣ ጠንካራ ክለቦች/ሊጎች እንዲፈጠሩ በአደረጃጀት፣ በአሰራር፣ በሰለጠነ የሰው
ኃይል … ወዘተ መጠናከር/ማጠናከር

6 የሴቶችን እግር ኳስ ማሳደግ – የሴቶች እግር ኳስን መሠረታዊ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ መልሶ በማደራጀት “ሴቶች ለሴቶች” በሚል መርህ መነሻነት የቢዝነስ እሴት የሚጨመርበትን አሰራር መዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግ፣ እንዲሁም ለሴቶች እግር ኳስ ጨዋታ ተሳታፊዎች የአቅም ግንባታ ፕሮግራም በመቅረጽና ተግባራዊ ማድረግ

7 የእግር ኳስን አዎንታዊ እሴት በመላዋ ኢትዮጵያ ማስረጽ – 5ቱን የስፖርት መርሖዎች በስፖርት ቤተሰቡ በማስረጽ ዘረኝነትና ሌሎች መድልኦዎችን ዋጋት፣ ፍትሃዊነትና የእርስ በርስ መከባበርን ማሳደግ፣ ከሚለከታቸው ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ሀገር አቀፍ ተቋማት ጋር የምክክር፣ የትብብርና አጋርነት ሥርዓት መዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግ

ለአንድ ሰዓት ሳያቋርጡ ገለፃቸውን የቀጠሉት አቶ መላኩ በስፍራው የተገኙ ጋዜጠኞች ጥያቄ ከማቅረባቸው በፊት የፕሬዝዳንታዊ እና የሥራ-አስፈፃሚ ምርጫው ቦታ ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ መቀየሩን ተከትሎ ይሄንን ብለዋል። “የቦታ ለውጥ ቢደረግም የትም ቢሆን እሄዳለው። ድምቢ ዶሎም ይሁን የትም ይሁን ለእኔ ችግር የለውም። ግን የተፈፀመበት ነገር አግባብ ነው የሚለው መመለስ አለበት። የተሄደበት አግባብ ልክ አይደለም። በግልም ራሴን ከምርጫው እንዳገል የሚያስደርገኝ ምክንያትም የለም። በአጠቃላይ መራጩ በገንዘብም ሆነ በሌላ ምክንያት ከሚመርጥ ለለውጥ መምረጥ። ፍትሃዊ ምርጫ ከሆነ ወደ ውጤት እመጣለው።” ብለዋል።

ከብዙሃን መገናኛ አባላት የቀረቡ ጥያቄዎች እና የተሰጡ ምላሾች

በምርጫው ላይ ገንዘብ ተፅዕኖ ሊፈጥር ስለመቻሉ እና በፍቃደኝነት ራሳቸውን ከምርጫ ውጪ ያደርጉ እንደሆን…

“በገንዘብ ሊሰራ ይችላል ፤ ይህን የሚለውን እገምታለሁ እጠብቃለሁ ፤ ‘የምርጫ ሂደቶች እንዴት ነበሩ ?’ የሚለውን ለማስቀመጥ ስሞክር። ከስጋትም የመነጨ ነው ፤ በአንዴ ይስተካከላል ብዬም ስለማላምን። ነገር ግን ተስፋዬ ምንድነው ለውጥ ያስፈልጋል በማሕበረሰቡ ፣ በሚዲያ ፣ በስፖርቱ ማህበረሰብ ፣ በተጫዋች ፣ በዳኛ ፣ በአሰልጣኝ ወዘተ በሚል ተስፋ ይጀምራል ብዬ ስለማስብ ስራዎች ደግሞ ግልፅ እንዲሆኑ ተገቢውን ክትትል አድርገን የምርጫ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ታዛቢዎች ግዴታቸውን እንዲወጡ በማድረግ። በህሊና ዳኝነትም ለውጥ እንዲመጣ እንፈልጋለን የሚል እንዲመጣ ነው። ሁለተኛ አሰራሩን ሁሉም አካል በንቃት እንዲከታተለው በማድረግ በአንዴ እንኳን ባናፀዳው በቀጣዩ ትውልድ እና ለቀጣዩ ሥራ ትምህርት ሆኖ እንዲያልፍ እንሰራለን ብዬ ስለማስብ ቢኖርም በምክንያት የሚመርጠው ማህበረሰብ ይበልጣል ብዬ ስለማስብ አሸንፋለሁ ብዬ ነው የማስበው። ራሴን አላገልም! አሁንም ቃሌን ደግሜ እሰጣለሁ ከምርጫው ራሴን አላገልም !”

በምርጫው ቢሸነፉ ከእግርኳሱ ይጠፉ እንደሆን…

“ምርጫ ማሸነፍ እና መሸነፍ እንዳለው ይታወቃል። ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ሌላ ሰው የሚወስደው ከሆነ ችግር የለብኝም። ለማገዝ ነው የምፈልገው። ፍትሀዊ ባልሆነ መንገድ ሲመጣ ግን ለማጋለጥ እሰራለሁ ከኳሱ ግን ልጠፋ አልችልም።”

በፋሲል ከነማ ቦርድ አባልነታቸው ወቅት ክለቡን ህዝባዊ ከማድረግ እና ሌሎች ጉዳዮች አንፃር ያላሳኳቸው ነገሮች ስለሚኖራቸው ተፅዕኖ…

“ፋሲል ላይ በደጋፊነት ከጀርባ ፋይናንሱ እንዲያድግ ስሰራ ቆይቻለሁ ፤ ከሌሎች ተደራራቢ ስራዎች ጋር። በቅርቡ ግን ለውጥ ያስፈልገዋል ብዬ ነው የገባሁት። ፕላናችንንም እያወጣን ነው። እዚህ አሁን ያነሳኋቸው ሀሳቦች ፋሲል ላይም እንዲደገሙ ነው የምንሰራው። ይሄ ለፋሲል ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ክለቦቻችን መስራት ያለብን የሁላችንም ሥራ ነው። ወደ ሕዝባዊነት የመቀየር እና ከመንግሥት ጥገኝነት የማውጣት ሥራ ያስፈልገናል ብለን ብንወስደው ጥሩ ይመስለኛል።”

የእግርኳሱ ዕድገት አሁን ስላለበት ደረጃ…

“የእግርኳሱ መለኪያ አንዱ የመጨረሻው ውጤት ነው። በውጤት የት ላይ ነው ያለነው የሚለውን ሁላችንም የምናውቀው ነው። ሁለተኛ ቅድም ለማንሳት ሞክሪያለሁ ፤ የፊፋ በያዝነውን ወር ከአፍሪካ 41ኛ ከዓለም 138ኛ ነን። ይሄ የእግርኳሳችንን ዕድገት ያሳያል። ሌላው ተተኪ ማፍራት ላይ ነው። አለን ወይ ? ማህበረሰቡ ኳስን ባህሉ አድርጎ እየሄደ ተከታታይ የሆነ ግብዓት እየሆነ ሲቀጥል ነው። እዚህም እዚያም ለውጦች የሉም እያልኩ አይደለም። በአቶ ሰውነት ጊዜ የደረስንበት ደረጃ የሚታወቅ ነው። አብርሀም መጥቶ አሁን ውበቱ ተቀብሎ የደረስንበት ደረጃ የምናውቀው ነው። ይሄን ከአጠቃላይ እና ሌሌች ከደረሱበት ድምር ስዕል ስንመዝነው ፣ የደጋፊዎቻችን እርካታ ስንመዝን ፣ የት ላይ ነው ያለነው የሚለውን ስናይ መሰረታዊ ለውጥ ያስፈልጋል የሚለው ተገቢ ይመስለኛል። መነሻ ግን የለንም እያልኩ አይደለም። መልካም ነገሮችን ወስደን የጎደሉትን መሙላት እያልኩ ነው የሄድኩት። ቅድም እሴቶች ብዬ ያስቀምጥኳቸው መሰርታዊ ናቸው። እግርኳሱም ላይ ቆጥረን እንስራባቸው ነው እያልኩ ያለሁት። እግርኳስ ገለልተኛ መሆን አለበት። ቅድም ከተጠየቀው አስተሳሰብ መፅዳት አለበት። እነዚህ እሴቶች ከእግርኳሱ አልፈው በሌሎች ስፖርቶች እና ሥራዎች ላይ በጎ ተፅዕኖ እንዲያሳድሩ መስራት አለብን።”

የምርጫው ቦታ ስለመቀየሩ…

“የትም ይሁን የት ጥያቄው የፍትሀዊነት ጉዳይ ነው። የተሰጠው ምክንያት ግን ውሃ የማይቋጥር እንደሆነ ሁላችንም እንገነዘባለን። እንደውም ቅድም ለተባለው ‘የገንዘብ እና የማታለል ሂደት አመቺ ቦታ እየተፈለገ ነው ወይ ?’ የሚል ስጋት አለን። እዛ ማጭበርበር አይቻልም ማለት ነው። በፊት ለምን እዛ ሄደ ? አሁን ለምን ተቀየረ ? ምን ስለተፈለገ? የከተማው ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊነት እወስዳለሁ በሚልበት ጊዜ ? ስለዚህ ሌላ ምክንያት ሊኖር ይችላል። ያ ምክንያት ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚመጡ የማይፈለጉ ተግባሮችን ለመከወን ነው የሚል ስጋት አለን። ያንን ግን ህዝቡ በመታገል እና አሰራሩን በመቃወም ሊደግፈው ይገባል። ይሄ የአንድ ፕሬዘዳንት እና የአንድ ክልል ጉዳይ አይደለም። የሀገር እና የእግርኳሳችን ትንሳኤ ጉዳይ ነው። የሁላችንም ነው ብለን ብንሰራበት ይጠቅማል።”

ያሰቧቸውን ለውጦች ስለሚያሳኩበት የጊዜ መጠን…

“ዕድገት ሂደታዊ ነው። በአራት ዓመት እነዚህ ሁሉ ይሳካሉ ማለት አይደለም። እንጀምራቻዋለን ፣ ውጤት ያስመዘግባሉ ፣ የቀጣዩ አራት ዓመት የሚመጣው ሰው ግን ከደህና መደላድል ተነስቶ መሄድ መቻል አለበት። ይሄ ዝርዝር አክሽን ፕላን ይሰራለታል። በየዓመቱ የምናሳካው በዝርዝር ዕቅዱ ውስጥ ይካተታል። የለውጥ መሪ ካለ ፣ ጥሩ ተከታይ ካለ እና ቀን እና ለሌሊት መስራት ከቻልን የምናሳካቸው ጉዳዮች ናቸው። ቀጣዩ የሚመጣው ደግሞ ዱላ ቅብብሉን ተከትሎ ለውጡን በማስቀጠል ወደተባለው ማማ ይዘን እንሄዳለን።”

የፕሬዘዳንትነት ቦታውን ወደ ሌላ ቦታ ለመሸጋገሪያነት ይጠቀሙበት እንደሆን…

“መሸጋገር ብፈልግ ድሮ ብዙ ቦታ መሸጋገር እችል ነበር። ግን ለሀገሬ የዕድገታችን ችግር የተቋም ግንባታ ችግር ነው ብዬ ስለማምን በህይወቴ የተወሰኑ ተቋማትን እሱ ገናባ መባልን ፣ የራሴን አሻራ ትቼ ማለፍ ነው የምፈልገው። ስለዚህ በእግርኳሱ ያንን አሻራ ትቼ ተተኪ ኃይል እያፈራን ሄደን ወደ ሚቀጥለው ልንሄድ እንችላለን። ነገር ግን መሸጋገሪያ ብዬ አላስበውም ፤ አላልመውም። አብሬያችሁ ግን ተቋም እቀይራለሁ ብዬ አምናለሁ። የኔ አሻራ ተቋማት ተቀይረው ሀገሬ ተቀይራ ማየት ነው። ከዛ ውጪ ትርፍ ነው። ያ ማለት ግን ወደ ቀጣይ የሥራ ደረጃ አልሸጋገርም ማለት አይደለም።”

በፌዴሬሽኑ እና በሊግ ካምፓኒው መካከል ስላለው ቁርሾ…

“ዞሮ ዞሮ መሰረታዊ መርሁ እኔ እስከማምንበት ድረስ የህዝብ እና የግል አብሮ መስራት የለውጥ መሰርት ነው። በመርህ ደረጃ መሰራት አለበት። ባለኝ መረጃ የሊግ ካምፓኒው እየሰራቸው ያላቸው ነገሮች መሰረታዊ ናቸው። እንዳውም አሰራሩ ወደ ሌሎች ሊጎችም መውረድ አለበት የሚል ሀሳብ አለኝ። በመተባበር እና በመደጋገፍ የሚሰሩ ሥራዎች ስላሉ ችግር የሚመስሉ የተንከባለሉ የሚመስሉ ነገሮችን መፍታትንም ይጨምራል። ብዙ ትርፍ የምናገኝባቸው መንገዶች እኮ አሉ። ስለምናውቃት እና ባለችን ስለምንጣላ እንጂ ሀብት ላይ ሆነን ስለድህነት የምንዘምር ህዝቦች ነን። ስለዚህ ሀብት እንዴት መመንጨት አለበት የሚለውን በበጎ ሀሳብ ከሰራን ለሁሉም የሚበቃ ሀብት መፈጠር ይችላል ብዬ ስለማምን ያሉ ችግሮችን እንቀርፋለን ብዬ ነው የማምነው። አሰራሩ ወደ ሌሎች ሊጎች አድጎ ፌዴሬሽኑ በልማት ፣ በመሰረት ልማት በዲፕሎማሲ እና በመሳሰሉት ከፍ ባሉ ሥራዎች ላይ እንዲያተኩር እና የዕለት ተዕለት ውድድር መከታተል ሥራዎች መውጣት ይገባቻዋል ብዬ አስባለሁ። እንጂ እኔ ገቢ የሚያጣላ አይመስለኝም ፤ ድህነት ነው የሚያጣለው። ያለችን እና የምናያት ምንጭ አንድ ትሆንና ድህነት ያጣላናል።”