የዘንድሮ የካጋሜ ካፕ ውድድር አይከናወንም

የቀጠናው ክለቦችን የሚያሳትፈው የሴካፋ ካጋሜ ካፕ የዘንድሮ ውድድር እንደማይደረግ የውድድሩ የበላይ አካል አስታውቋል።

1974 በይፋ እንደተጀመረ የሚነገረው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ የክለቦች ውድድር ከ2002 ጀምሮ በሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ስፖንሰር አድራጊነት ካጋሜ ካፕ በሚል ስያሜ እየተከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል። በዞኑ የሚገኙ የሊግ አሸናፊዎችን ነገርግን እንደየሀገራቱ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የውስጥ አሰራር የጥሎ ማለፍ እንዲሁም የደረጃ ተፋላሚዎችን የሚያሳትፈው ውድድሩ በተለያዩ ጊዜያት ያልተከናወነበት ወቅት የነበረ ቢሆንም የዘንድሮውን 46ኛ የውድድር ዓመት በታንዛኒያ አስተናጋጅነት ለማከናወን ታስቦ እንደነበር መገለፁ ይታወቃል። ነገርግን ከደቂቃዎች በፊት በወጣ መረጃ ሴካፋ የዘንድሮ ውድድር እንደማይከናወን ገልጿል።

ሴካፋ በዋና ዳይሬክተሩ አውካ ጌቺዮ አማካኝነት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት አባል ሀገራት በፊፋ እና ካፍ ውድድሮች የተወጠሩ በመሆኑ እና ውድድሩን ለማከናወን ነፃ ጊዜ ማግኘት አዳጋች በመሆኑ የዘንድሮ ውድድር አይደረግም።

ሀገራችን ኢትዮጵያ እስከ 2008 ድረስ ክለቦችን በዚህ ውድድር ያካፈለች ሲሆን 2002 ላይ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ በውድድሩ ለፍፃሜ በመድረስ (በሩዋንዳው ኤ ፒ አር ተረቶ ዋንጫ ሳያገኝ ቀረ) የሀገራችን ብቸኛው ባለታሪክ ክለብ እንደሆነም ይታወቃል።

ከሴካፋ ውድድሮች ጋር በተያያዘ ሀገራችን ኢትዮጵያ የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ውድድርን ከመስከረም 20 እስከ ጥቅምት 4 ድረስ እንደምታስተናግድ ይታወቃል።