መቻል የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፅሟል

ስብስቡን እንደ አዲስ እያዋቀረ የሚገኘው መቻል ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል።

በቀጣዩ የውድድር ዓመት በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እየተመራ ሊጉን የሚቀርበው መቻል እስካሁን የ14 ተጫዋቾችን ዝውውር የፈፀመ ሲሆን አሁን ደግሞ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን አግኝቶ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እየከወነ እንደሚገኝ አውቀናል።

ቡድኑን በአንድ ዓመት ውል የተቀላቀለው የመጀመሪያው ተጫዋች በኃይሉ ግርማ ነው። በኃይሉ ከሙገር ሲሚንቶ ተነስቶ በመከላከያ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በመጫወት ያሳለፈው ሲሆን የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በሰበታ ከተማ ማሳለፍ ከቻለ በኋላ ቀጣይ መዳረሻው ሀዲያ ሆሳዕና እንደሆነ በክለቡ በኩል መረጃ ይፋ ሆኖ የነበረ ቢሆንም ተጫዋቹ ህጋዊ መስፈርቶችን በሟሟላት ፊርማውን ለመቻል ማኖሩን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ ደሳለኝ ከተማ ነው። በመስመር እና መሐል ተከላካይ ቦታ እንዲሁም በተከላካይ አማካይ ቦታ መጫወት የሚችለው የቀድሞ የአውስኮድ ተጫዋች የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በአራዳ ካሳለፈ በኋላ የእግርኳስ ህይወቱን በመቻል ለመቀጠል የሁለት ዓመት ውል ፈርሟል።

መቻል በአጠቃላይ አህመድ ረሺድ ፣ ቶማስ ስምረቱ ፣ ተስፋዬ አለባቸው ፣ ከነዓን ማርክነህ ፣ ምንይሉ ወንድሙ ፣ ዳግም ተፈራ ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ ፣ በረከት ደስታ ፣ ፍፁም ዓለሙ፣ ውብሸት ጭላሎ፣ የአብስራ ሙሉጌታ፣ በኃይሉ ኃይለማርያም፣ ተክለማርያም ሻንቆ እና ግርማ ዲሳሳን ማስፈረሙ ይታወቃል።