ሁለት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ለቻን ውድድር ቅድመ ስልጠና ወደ ካይሮ ያመራሉ

በአልጄሪያ አስተናጋጅነት የሚከናወነው የቻን ውድድርን የተመለከተ የቅድመ ስልጠና ተካፋይ ለመሆን ሁለት የሀገራችን ዳኞች የፊታችን ዕሁድ ወደ ግብፅ ያመራሉ።

በአፍሪካ እግር ኳስ የበላይ አካል በሆነው ካፍ አዘጋጅነት በሀገር ውስጥ ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ተሳታፊ የሚያደርገው የቻን ውድድር በቀጣዩ ዓመት በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በወርሀ ጥር ይደረጋል፡፡ በውድድሩ የሚሳተፉ ሀገራት በማጣሪያ መርሐ-ግብር ላይ እየተሳተፉ የሚገኝ ሲሆን ውድድሩን በዳኝነት ለሚመሩ ዳኞች ካፍ አስቀድሞ የሜዳ እና የቫር ስልጠናን ለመስጠት ከተለያዩ ሀገራት ለመረጣቸው ዳኞች ጥሪ ሲያቀርብ ሁለት ኢትዮጵያዊያንም በጥሪው መካተታቸው ታውቋል።

በተለያዩ አህጉራዊ እና አለምአቀፍዊ መድረኮች ላይ ኢትዮጵያን ወክላ በመዳኘት የምናውቃት እና ከሰሞኑ በህንድ አዘጋጅነት ለሚደረገው የአለም ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ ላይ በቫር ዳኝነት ግልጋሎት እንቅትሰጥ ጥሪ የደረሳት ሊዲያ ታፈሰ በተመሳሳይ በቻን ውድድር ላይ በቫር ዳኝነት ማገልገል እንድትችል በስልጠናው ስትካተት ሌላኛው ኢትዮጵያዊ የመሀል ዳኛ በላይ ታደሠም ውድድሩን በመሀል ዳኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ መምራት እንዲችል በቅድመ ስልጠናው ተካፋይ እንዲሆን መጠራቱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

ሁለቱም ዳኞች ለስልጠናው ብቁ ሆኖ ለመገኘት በጋራ በመሆን ልምምዳቸውን በመስራት ላይ የሚገኙ ሲሆን የፊታችን ዕሁድም ወደ ግብፅ ካይሮ ያቀናሉ፡፡