ከፍተኛ ሊግ | ደሴ ከተማ አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈረመ

በቅርቡ አዲስ አሰልጣኝ የቀጠረው ደሴ ከተማ አስራ ሰባት ተጫዋቾችን የስብስቡ አካል አድርጓል፡፡

ከአንድ ዓመት በኋላ ዳግም ወደ ውድድር ለመመለስ አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃን በዋና አሰልጣኝነት የቀጠረው ደሴ ከተማ ራሱን ማጠናከር ጀምሯል፡፡ በ2013 የውድድር ዘመን በክለቡ የነበሩ ተጫዋቾችን ጨምሮ ከተለያዩ ክለቦች በድምሩ አስራ ሰባት ተጫዋቾችን የቡድኑ አካል ያደረገ ሲሆን በቀጣይ በቀናቶች ውስጥ ተጨማሪ ተጫዋቾችን እንደሚያስፈርም ክለቡ የላከልን መረጃ ይጠቁማል፡፡

በሀዋሳ ከተማ ፣ ፋሲል ከነማ ፣ ሀምበሪቾ ከተማ እንዲሁም የተጠናቀቀውን ዓመት በስልጤ ወራቤ ጀምሮ በውሰት በአዳማ ያጠናቀቀው አማካዩ ፀጋአብ ዮሴፍ እና በደቡብ ፓሊስ ፣ ድሬዳዋ ከተማ ፣ ሀዋሳ እና ገላን የተጫወተው አማካዩ ምስጋናው ወልደዮሐንስን ሲፈርሙ በደደቢት ፣ ወልቂጤ ከተማ እና አምና በመከላከል በመጫወት ያሳለፈው አጥቂው አክዌር ቻሞ እንዲሁም በቤንች ማጂ ቡና ያሳለፈው አማካዩ ቶስላች ሳይመን ወደ ቀድሞ ክለባቸው የተመለሱበትን ዝውውር ፈፅመዋል።


በተጨማሪም ክለቡ በ2013 በስብስቡ የነበሩ ተጫዋቾች በአዲስ መልክ አስፈርሟል። በዚህም በግብ ጠባቂ ቦታ እድሪስ አብዱ እና እስራኤል አለ ፣ በተከላካይነት አብዱልአዚዝ ዳውድ ፣ አንዋር መሀመድ ፣ ሳሙኤል ወንድሙ እና በረከት አድማሱ፣ አማካይ ላይ ብርሀን በላይ ፣ አብደላ እሸቱ ፣ በድሉ መርዕድ ፣ ሀብታሙ ፈቀደ ፣ ሙሉቀን አሰፋ እና አብዱሰላም የሱፍ በአጥቂ ስፍራ ላይ ደግሞ አማኑኤል ቺፖ የክለቡ አዳዲሶቹ ፈራሚዎች ሆነዋል።