ኢትዮ ኤሌክትሪክ በድጋሚ አሰልጣኙን ጠርቷል

ከሳምንት በፊት ከአሰልጣኙ ጋር ውይይት ያደረገው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዳግመኛ አሰልጣኙን መጥራቱ ታውቋል።

በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቀናት በፊት ዋና አሰልጣኙን እና የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኙን በመጥራት ውይይት ማድረጉ ይታወሳል። አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና የቡድኑን ውጤት በቶሎ የማስተካከል መመርያ ተቀበልው ወደ ድሬደዋ እንዲመለሱ ሲደረግ ቡድን መሪው እና የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ዝቅ ብለው እንዲሰሩ ውሳኔ መተላለፉም መዘገባችን አይዘነጋም።

አሁን ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሰረት አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና በድጋሚ በክለቡ ጥሪ ተላልፎላቸው ዛሬ በማምሻው በረራ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ መሆኑን አውቀናል። ነገ ከክለቡ አመራሮች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ የሰማን ሲሆን ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮቻችን እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ አሰልጣኙ በድሬደዋ ያጋጠማቸው ተከታታይ ሽንፈት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የነበራቸው ጉዞ ማብቂያ ሊሆን ይችላል።

ነገ የሚኖረውን ውይይት ተከትሎ የሚወጡ መረጃዎች ተከታትለን የምናቀርብ ይሆናል።