ከፍተኛ ሊግ | እንጅባራ ከተማ አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ የመጀመሪያ ዓመት ተሳትፎውን ዘንድሮው የሚያደርገው የአሰልጣኝ አዲሱ ዶይሶው እንጅባራ ከተማ አስር አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በ2013 ክረምት ወር በተደረገው የአንደኛ ሊግ ማጠቃለያ ውድድር ተሳትፎ የማደግ ዕድልን ያገኘው እንጅባራ ከተማ የተጠናቀቀውን ዓመት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር መነሻነት በከፍተኛ ሊጉ ሳይሳተፍ መቅረቱ የሚታወስ ሲሆን ዘንድሮ ግን በሊጉ ላይ ከሚወዳደሩ ክለቦች አንዱ በመሆን ብቅ ብሏል፡፡ ቡድኑን ያሳደገውን አሰልጣኝ አዲሱ ዶይሶን ኮንትራት ክለቡ ለተጨማሪ ዓመት ካራዘመ በኋላ የአስር አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር በመፈፀም እና የነባሮችን ውል በማራዘም ዝግጅቱን ቀጥሏል፡፡

የቡድኑ አዳዲስ ተጫዋቾች ዳግም አራጌ ግብ ጠባቂ ከቂርቆስ ፣ ተስፋፅዮን ፋንቱ ተከላካይ ከኤሌክትሪክ ፣ ይበልጣል ሽባባው ተከላካይ ከወልቂጤ ፣ ሀብታሙ መዝገቡ ተከላካይ ከወራቤ ፣ ሀብታሙ ጥላሁን አማካይ ከኤሌክትሪክ ፣ ነፃነት ወርቁ አማካይ ከቡታጅራ ፣ ምትኩ ማመጫ ተከላካይ ከሀላባ ፣ አበበ ታደሰ አጥቂ ከካፋ ቡና ፣ አብርሃም አሰፋ አጥቂ ከኮልፌ እና ሙከረም አለቱ አጥቂ ከቂርቆስ የክለቡ አዳዲስ ፈራሚዎች ሆነዋል፡፡