ሪፖርት | ዐፄዎቹ ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል

ሦስት ነጥብ ካገኙ ሦስት ጨዋታዎች ያለፋቸው ፋሲል ከነማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ሦስት ጎሎች ከድል ጋር ታርቀዋል።

በ7ኛ የጨዋታ ሳምንት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር አንድ አቻ የተለያዩት ፋሲል ከነማዎች ከፍልሚያው የአንድ ተጫዋቾች ለውጥ ብቻ በማድረግ ዛሬ ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ አርፎ ሀብታሙ ገዛኸኝ ቀዳሚውን አሰላለፍ እንዲተዋወቅ ተደርጓል። ለገጣፎ ለገዳዲዎች በበኩላቸው በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት ለወልቂጤ ከተማ ሦስት ግብ እና ነጥብ ካስረከቡበት ጨዋታ ኦካይ ጁል የአንዋር አብዱልጀባርን እንዲሁም ብሩክ ብርሃኑ የአስናቀ ተስፋዬን ቦታ ተክተው ጨዋታውን አስጀምረዋል።

ጥሩ ፉክክር ማሳየት የጀመረው ጨዋታው በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች እምብዛም የግብ ሙከራዎች ባይበረክቱበትም የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራስ ለማድረግ ሲሞከር የነበረበት መንገድ መልካም የሚባል ነበር። እስከ 33ኛው ደቂቃ ድረስም አንድ ጥቃት ብቻ ተደርጎበታል። በዚህም ገና በ4ኛው ደቂቃ ከረጅም ኳስ መነሻን ባደረገ አጋጣሚ ካርሎስ ዳምጠው ሳጥኑ ጫፍ ላይ በመሆን ጥብቅ ኳስ ወደ ግብ ልኮ የመጀመሪያ ዒላማውን የሳተ አጋጣሚ ተስተናግዷል። ከላይ በጠቀስነው 33ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ይሁ ግዙፍ አጥቂ ካርሎስ ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ የተገናኘበትን አጋጣሚ ከተፈራ አንለይ አግኝቶ ግብ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ሚኬል ሳማኬ በድንቅ ሁኔታ ዕድሉን አምክኖታል።

ለካርሎስ ሁለተኛ ሙከራ ምላሽ ለመስጠት ወዲያው በቁጥር በዝተው የወጡት ፋሲሎችም የመስመር አጥቂዎቻቸው ሽመክት እና ሀብታሙን ቦታ አቀያይረው ባደረጉት ፈጣን የመስመር ላይ ሽግግር ለመጀመሪያ ጊዜ ለግብ ቀርበው ነበር። በዚህም ሀብታሙ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ሽመክት በሩቁ ቋሚ አግኝቶት መዳረሽያውን መረብ ላይ ለማድረግ ቢጥርም ግብ ጠባቂው ሚኪያስ ዶጂ አድኖበታል። ከደቂቃ በኋላም በተመሳሳይ ከመስመር የተሻማን ኳስ የመሐል አጥቂው ፍቃዱ ዓለሙ በግንባሩ ለማስቆጠር ዳድቶ ወጥቶበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ የዕለቱ አራተኛ ዳኛ ጭማሪ ደቂቃ በሚያሳዩበት ቅፅበት ደግሞ ሀብታሙ በቀኝ የሳጥኑ ክፍል ጥሩ ኳስ ወደ ግብ መትቶ ተከላካዮች ከመስመር ላይ መልሰውበታል።

ሁለተኛውን አጋማሽ በጥሩ ሁኔታ የጀመሩት ፋሲል ከነማዎች የኳስ ቁጥጥራቸውን በዓላማ በማድረግ በላይኛው የሜዳ ክልል በተደጋጋሚ ለመገኘት ሲጥሩ ነበር። በ54ኛው ደቂቃ ግን መሐመድ አበራ ከግራ መስመር ሰብሮ በመግባት በሞከረው ኳስ ግብ ለማስተናገድ ተቃርበው ሳማኪ አድኗቸዋል።

ግጥግጥ ብሎ በመከላከል ለፋሲል ተጫዋቾች ቦታ ላለመስጠት በመጣር ረጃጅም ኳሶችን ለካርሎስ በመጣል አንደኛ እና ሁለተኛ ፍልሚያዎችን እያሸነፉ ጥቃቶችን መሰንዘር የመረጡት ለገጣፎ ለገዳዲዎች እስከ 68ኛው ደቂቃ ድረስ ጨዋታው በሚፈልጉት መንገድ ቢሄድም በ73ኛው ደቂቃ በፋሲል ማንኳኳት በራቸውን ከፍተዋል። በዚህም ከአስር ደቂቃዎች በፊት ሀብታሙን ቀይሮ የገባው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከግራ የሳጥኑ ክፍል አክርሮ በመታው ኳስ ፋሲል ከነማ መሪ ሆኗል።

ይህ ጎል የበለጠ ያነቃቸው ፋሲሎች በ80ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር በተነሳ እና ፍቃዱ መሬት ለመሬት በሞከረው ኳስ መሪነታቸውን ሊያሳድጉ ነበር። ለገጣፎዎች ግቡ እንደተቆጠረባቸው የአጥቂ አማካይ እና አጥቂ በመቀየር ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢጥሩም ውጥናቸው ሳይሰምር ቀርቷል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለጊዜው ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ናትናኤል ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመሩት ሦስት ደቂቃዎች አጋማሽ ላይ ደግሞ ፍቃዱ ዓለሙ ከቀኝ መስመር ሽመክት ጉግሳ ያሻማውን ኳስ በግንባሩ ወደ ግብነት ቀይሮት የጨዋታው የማሳረጊያ ግብ ተገኝቷል።