ፋሲል አስማማው ለሳምንታት ከሜዳ ይርቃል

በትናቱ አመሻሽ ጨዋታ ከበድ ያለ ጉዳት ያስተናገደው የባህር ዳር ከተማው አጥቂ ፋሲል አስማማው ለሳምንታት ከሜዳ እንደሚርቅ ታውቃል።

በዘንድሮ የውድድር ዘመን ከለገጣፎ ለገዳዲ የጣና ሞገዶችን የተቀላቀለው ወጣቱ አጥቂ ፋሲል አስማማው በአሰልጣኝ ደግያረጋል ይግዛው ታምኖበት ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የመጀመርያ ተመረጭ በመሆን ዕድሎችን እያገኘ ይገኛል። ምንም እንኳን በተጫወተባቸው ጥቂት ጨዋታዎች እስካሁን ለአዲሱ ክለቡ በስሙ ጎል ባያስቆጥርም ዕድሎችን በመፍጠር ክለቡን እያገዘ ይገኛል።

ተጫዋቹ ባህር ዳሮች በትናትናው ምሽት አዳማ ከተማን አንድ ለምንም በመርታ ወደ መሪዎቹ በቀረቡበት ጨዋታ በመጀመርያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃ የግራ እጁ ትከሻ ላይ ውልቃት በማጋጠሙ ለተሻለ ህክምና በአንቡላንስ ወደ ሆስፒታል በፍጥነት መወሰዱ ይታወሳል።

ዛሬ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ምርመራ ያደረገው ፋሲል ጉዳቱ ብዙ የሚያሰጋው እንዳልሆነ እና ለሦስት ሳምንታት የህክምና ክትትል ካደረገ በኋላ ወደ መደበኛ ልምምድ መመለስ እንደሚችል ተገልፆለታል። ይህን ተከትሎ የጣና ሞገዶቹ እስከ አንደኛው ዙር መጠናቀቂያ ድረስ የአጥቂያቸውን ግልጋሎት የማያገኙ ይሆናል።

በሌላ የጉዳት ዜና በተመሳሳይ በትናትናው ጨዋታ በጉዳት ተቀይሮ የወጣው አማካይ ፉአድ ፈረጃ ጉዳቱ የከፋ ባለመሆኑ ለቀጣዩ ጨዋታ እንደሚደርስ ሰምተናል።