ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ9ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ9ኛ የጨዋታ ሳምንት በአንፃራዊነት የተሻለ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾችን እንደሚከተለው መርጠናል።

የተጫዋች አደራደር ቅርፅ : 4-1-3-2

ግብ ጠባቂ


ዳንኤል ተሾመ – ድሬዳዋ ከተማ

ዳንኤል ድሬዳዋ ከተማ ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ሦስት ነጥብ ሲወስድ ያሳየው ብቃት ጥሩ የሚባል ነው። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኑ 0ለ0 በነበረበት ሰዓት ፈጣኖቹ የመድን አጥቂዎች የሞከሯቸውን ወሳኝ ኳሶች ሲያመክን ነበር። ከምንም በላይ በ28ኛው ደቂቃ ሲሞን ፒተር ወደ ግብ መትቶት የመለሰው ኳስ ቡድኑ በጨዋታው እንዲቆይ አድርጓል።

ተከላካዮች


አሰጋኸኝ ጼጥሮስ – ድሬዳዋ ከተማ

እንየው በቅጣት ምክንያት ከሜዳ ከራቀ በኋላ የእርሱን ቦታ የተካው አሰጋኸኝ በየጨዋታው አዎንታዊ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል። በተለይ በመከላከሉ ረገድ ለመድን የመስመር ጥቃት ተገቢ ምላሽ እየሰጠ የተጋጣሚን የማጥቃት አጨዋወት ሲያመክን ውሏል። በተቃራኒ በእርሱ ቦታ የነበረው ኪቲካ ጅማም ገና በ55ኛው ደቂቃ ተቀይሮ እንዲወጣ ያስገደደ ብቃት አሳይቶ ቦታውን አስከብሮ ወጥቷል።

አሳንቴ ጎድፍሬድ – ድሬዳዋ ከተማ

በመቀመጫ ከተማው ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ የሚገኘው ድሬዳዋ ቡድን ውስጥ መልካም ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው አንደኛው ተጫዋች ጎድፍሬድ ነው። በተለይ በአንድ ለአንድ ግኝኙነቶች የተሻለ የነበረ ሲሆን ወደ ሳጥን የሚላኩ ኳሶችንም አደጋ ከመፍጠራቸው በፊት እየደረሰ ሲያመክን ነበር። ቡድኑን ከአቻ ወደ አሸናፊ ቦታ ያሸጋገረች እጅግ ወሳኝ የግንባር ጎልም ባለቀ ሰዓት አስቆጥሯል።

ያኩቡ መሐመድ – ሲዳማ ቡና

ዘንድሮ የወጥነት ችግር ያለበት ያኩቡ ባሳለፍነው ሳምንት ቡድኑ መቻልን ሲረታ አንድም ግብ እንዳይስተናገድበት የበኩሉን ሲወጣ ተመልክተነዋል። ተጫዋቹ በዐየርም ሆነ በመሬት ላይ ፍልሚያዎች ድንቅ የነበረ ሲሆን የተከላካይ ክፍሉንም እንደ አምበል በመምራት እና የኳስ ምስረታው ላይ አበርክቶ በመስጠት የተዋጣለት ጊዜ አሳልፏል።

ኃይለሚካኤል አደፍርስ – ኢትዮጵያ ቡና

በተለየ የተጫዋች አደራደር ቅርፅ ወደ ሜዳ በገባው የኢትዮጵያ ቡና ስብስብ የመስመር ተመላላሽ (Wing Back) ኃላፊነት እንዲወጣ የተደረገው ኃይለሚካኤል በ81ኛው ደቂቃ ተጎድቶ ተቀይሮ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ ነበር። የግራ መስመሩን መልካም በሚባል ብርታት የሸፈነ ሲሆን መሐመድኑር ያስቆጠረውን የመጀመሪያ ጎልም አመቻችቶ አቀብሏል።

አማካዮች


ጋቶች ፓኖም – ቅዱስ ጊዮርጊስ

የተከላካይ አማካዩ ጋቶች በሀዋሳው ጨዋታ ኮከብ የሚያስብለው እንቅስቃሴ በማሳየቱ በምርጥ ቡድናችን ቦታ አግኝቷል። ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጪ ጠንካራ የነበረው ጋቶች ሁለተኛው የቡድኑን ግብ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ሀዋሳዎች እንደልባቸው ጥቃቶችን እንዳይሰነዝሩ ተገቢውን የመከላከል ሽፋን እየሰጠ ሲጫወት ነበር።

ሽመክት ጉግሳ – ፋሲል ከነማ

ሌላኛው በምርጥ ቡድናችን ውስጥ ያካተትነው ተጫዋች ሽመክት ጉግሳ ነው። የመስመር አጥቂው ቡድኑ ጥሩ ባልነበረበት የመጀመሪያው አጋማሽም በግሉ የተሻለ የማጥቃት ሂደቶችን እያስመለከተ ነበር ፤ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ የቡድኑ የማጥቃት ኃይል ሲያድግ የበለጠ በመጉላት ለአንድ ጎሎች መቆጠር ቀጥተኛ አበርክቶ አድርጓል።

ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ – ፋሲል ከነማ

በጨዋታ ሳምንቱ ያነሰ ደቂቃ በሜዳ ላይ አሳልፈው ውጤት ቀያሪ እንቅስቃሴ ካደረጉ ተጫዋቾች መካከል ናትናኤል ቀዳሚው ነው። ተጫዋቹ በ62ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ገዛኸኝን ቀይሮ ወደ ሜዳ ከገባ በኋላ ፈጣን ሩጫዎችን በማድረግ ቡድኑን ለመጥቀም ሲጥር የነበረ ሲሆን በ13 ደቂቃዎች ልዩነትም በቀኝ እና በግራ እግሩ ቡድኑን ወደ አሸናፊነት ወስዷል። ተቀዛቅዞ የነበረው የቡድኑ የማጥቃት ኃይልም እንዲያድግ ከፍ ያለ ስራ ከውኗል።

ዱሬሳ ሹቢሳ – ባህር ዳር ከተማ

በባህር ዳር ከተማ ወሳኝ ተጫዋች እየሆነ የመጣው ዱሬሳ ቡድኑ ከፈታኙ የአዳማ ፍልሚያ ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ ያስቻለች ኳስ ከመረብ አገናኝቷል። ፈጣኑ ተጫዋች ገና በጨዋታው ጅማሮ ወሳኙዋን ግብ ያስቆጠረ ሲሆን ሌሎች ተመሳሳይ ፈጣን ሩጫዎችንም በማድረግ ለቡድኑ የግብ ምንጭ ሲሆን ነበር። ከኳስ ውጪም የአዳማን ተከላካዮች ለስህተት እየዳረገ አደጋን ለመፍጠር ሲንቀሳቀስ ታይቷል።

አጥቂዎች


ቻርለስ ሙሴጌ – ድሬዳዋ ከተማ

በምርጥ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው ሙሴጌ በፈታኙ የመድን ጨዋታ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገች ጎል በድንቅ ሁኔታ አስቆጥሯል። በወረቀት ላይ ከመስመር የሚነሳው ተጫዋቹ በእንቅስቃሴ ወደ መሐል እየገባ በተጋጣሚ ሳጥን አማራጭ ለመስጠት የሚጥር ሲሆን በጨዋታ ሳምንቱም የክለቡ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነበትን 5ኛ ጎል በስሙ አስመዝግቧል።

መሐመድኑር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና

አዲሱ ክለቡን ለመላመድ እየተቸገረ መስሎ የነበረው መሐመድኑር በ9ኛው የጨዋታ ሳምንት በቡናማዎቹ መለያ ግብ ማስቆጠር ጀምሯል። በርከት ያሉ ጨዋታዎችን ከመስመር እንዲነሳ ኃላፊነት ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን በዚህ ሳምንት ግን ከብሩክ ጎን ሁለተኛ አጥቂ ሆኖ ተሰልፎ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። ተጫዋቹም የቦታ አያያዝ እና አጨራረስ ብቃቱን እያሳደገ እንደመጣ በሁለቱ ጎሎች ታይቷል።

አሠልጣኝ


ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ፈረሰኞቹ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ሲመለሱ የቀድሞ ኃያልነታቸውን አግኝተው የጨዋታውን ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው ሲጫወቱ የነበረበት መንገድ የቡድኑን አሠልጣኝ የሳምንቱ ምርጥ እንድናደርግ አድርጎናል። በተለይ የቡድኑ መገለጫ የሆነው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ጥቃት ተመልሶ በ32 ደቂቃዎች ውስጥ ሦስት ነጥብ የወሰዱበትን ሦስት ግቦች አግኝተዋል። ይህንን ተከትሎም አሠልጣኝ ዘሪሁን ዮርዳኖስ እና ተመስገንን በመብለጥ ቀዳሚውም ቦታ አግኝተዋል።

ተጠባባቂዎች

ባህሩ ነጋሽ
ተስፋዬ ታምራት
አምሳሉ ጥላሁን
ኤሊያስ አህመድ
ፍሬው ሰለሞን
ቢኒያም በላይ
እስማኤል ኦሮ-አጎሮ
አማኑኤል ገብረሚካኤል