ባህር ዳር ከተማ ቅጣት ተጣለበት

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የውድድር አመራር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ ባህር ዳር ከተማ ላይ የገንዘብ ቅጣት አስተላልፏል።

የውድድሩ የበላይ አካል ከደቂቃዎች በፊት በማኅበራዊ ገፁ ላይ የውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ አርብ ታህሳስ 7 ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ከዳኞች እና ታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማስተላለፉን ይፋ አድርጓል።

የመቻሉ ተጫዋች ምንይሉ ወንድሙ ከጨዋታ በኋላ ዳኛን አፀያፊ ስድብ በመሳድብ በቀይ ካርድ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ስለመሆኑ ሪፖርት ስለቀረበበት ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 3 ጨዋታ እንዲታገድ እና በተጨማሪ የ3 ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ተወስኗል።

ባህርዳር ከተማ ከሲዳማ ቡና ጋር ባደረገው ጨዋታ የባህርዳር ከተማ ቡድን አምስት በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 5 ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ሲወሰን ከደጋፊዎች ጋር በተገናኘ ደግሞ የጨዋታ ሳምንቱ ከፍ ያለ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎበታል።

በዚህም ባህር ዳር ከተማ ከሲዳማ ቡና ጋር በነበረው የ12ኛ ሳምንት ጨዋታ የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች የዕለቱን ዋና ዳኛ አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት በመቅረቡ ደጋፊዎቹ በዕለቱና ከዚህ በፊት ተሳድበው በተቀጡት ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 75 ሺ ብር እንዲከፍል ተወስኗል።