የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከመንግሥት ድጋፍ ጠየቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቻን ለሚያደርገው ተሳትፎ ፌዴሬሽኑ ከመንግሥት ምን ያህል የፋይናንስ ድጋፍ እንደጠየቀ ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጪው ጥር በአልጄሪያ አስተናጋጅነት የሚከናወነው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ላይ እንደሚሳተፍ ይጠበቃል። ከውድድሩ ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስተዳደራዊ ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑ ከደቂቃዎች በፊት በድረ ገፁ አስታውቋል።

ፌዴሬሽኑ እንዳስነበበው ብሔራዊ ቡድኑ በውድድሩ ላይ ለሚኖረው ተሳትፎ ለቅድመ ዝግጅት እና ከውድድሩ ጋር ተያያዥ ለሆኑ ወጪዎች ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም የሚያስፈልግ በመሆኑ ለኢፌዲሪ መንግሥት የ50 ሚልዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደረግለት መጠየቁን አስታውቋል። ተቋሙ ከመንግሥት በጎ ምላሽ እየጠበቀ ከመሆኑ ባሻገር ተጨማሪ የፋይናንስ ምንጮችን በመፈለግ ላይ እንደሚገኝም ጨምሮ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮንሺፕ ላይ ለመሳተፍ የሚያደርገው ዝግጅት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለዚሁ ዝግጅት ሲባል ከሚቋረጥበት ታህሳስ 17 ጀምሮ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።