አዳማ ከተማ እግድ ተጥሎበታል

በቀድሞ ተጫዋቹ አቤቱታ ቀርቦበት የነበረው የሊጉ ክለብ አዳማ ከተማ በተጫዋቾች የዝውውር መስኮት እንዳይሳተፍ እግድ ተላልፎበታል።

የቀድሞ የአዳማ ከተማ 28 ተጫዋቾች በ19/02/12 እና 10/07/2013 ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ባስገቡት አቤቱታና ከሀያ ስምንቱ መካከል ዘጠኙ ክሱ እንዲንቀሳቀስ በጠየቁት መሠረት ክለቡ የ2011 የግንቦት እና ሰኔ ወር ደሞዝ እንዲከፍል ተጠይቆ እንደነበር ይታወሳል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴም በቀረበው አቤቱታ መሰረት የክለቡን ምላሽ አድምጦ በ27/11/2013 የተጫዋቾቹን ደሞዝ እንዲከፍል ውሳኔ አስተላልፎ ነበር። ነገርግን ከእነዚህ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ዱላ ሙላቱ ከህግ አማካሪው እና ጠበቃው አቶ ብርሃኑ በጋሻው ጋር በመሆን በ01/03/2015 ውሳኔው ተፈፃሚ አለመሆኑን አሳውቆ ክለቡ ላይ አዲስ ውሳኔ ተላልፏል።

በዚህም ክለቡ በተሰጠው ቀነ ገደብ የተላለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ ባለማድረጉ ከቀጣዩ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ጀምሮ እንዲታገድ ተወስኗል።