የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ስብስቧን ይፋ አድርጋለች

በቻን ውድድር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በአንድ ምድብ የምትገኘው ሞዛምቢክ ስብስቧን አሳውቃለች።

የ2023 የቻን ውድድር በቀጣዩ ወር በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር አልጄሪያ የሚካሄድ ሲሆን በዚህ መድረክ የምትካፈለው ሀገራችን ኢትዮጵያም በምድብ አንድ ከአዘጋጇ አልጄሪያ፣ ሞዛምቢል እና ሊቢያ ጋር መደልደሏ ይታወቃል። በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ብሔራዊ ቡድናችንም ከቀናት በፊት ለ42 እጩ ተጫዋቾች ጥሪ አድርጎ የነበረ ሲሆን በምድቡ የምትገኘው ሞዛምቢክም ከኢትዮጵያ በመቀጠል በውድድሩ የምትጠቀማቸውን ተጫዋቾች እንደለየች ይፋ ሆኗል።

በአሠልጣኝ ቼኪኒዮ ኮንዴ የሚሰለጥነው የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን ለውድድሩ ሦስት የግብ ዘቦች፣ ስምንት ተከላካዮች፣ ስድስት አማካዮች እና ስድስት አጥቂዎችን በአጠቃላይ 23 ተጫዋቾችን መምረጡ ተገልጿል።