ከፍተኛ ሊግ | የ11ኛ ሳምንት የሁለተኛ የቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 11ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ዘጠኝ ጨዋታዎች ሲፈፀም አምስቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

በቶማስ ቦጋለ ፣ ጫላ አቤ እና ተመስገን ብዙ ዓለም

የ04:00 ጨዋታዎች

በምድብ \’ሀ\’ ባህር ዳር ላይ የባቱ ከተማ እና የዱራሜ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ዱራሜዎች የተሻለ ተጭነው ለመጫወት ቢሞክሩም ባቱዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመመለስ ብልጫውን ወስደዋል። የተሻሉ የግብ ዕድሎች ባልተፈጠሩበት አጋማሽ በባቱዎች በኩል 3ኛው ደቂቃ ላይ ኢዩኤል ሳሙኤል ከቅጣት ምት የመታውና በተከላካዮች ተጨርፎ የላዩን አግዳሚ ታክኮ የወጣው ኳስ በዱራሜዎች በኩል ኪሩቤል ካሳ ከሳጥን ውጪ የመታውና እና ግብጠባቂው በቀላሉ የያዘው ኳስ የተሻሉ ሙከራዎች ነበሩ።

\"\"

ከዕረፍት መልስም በኳስ ቁጥጥሩ የበላይነቱን ለመውሰድ ጥሩ ፉክክር ቢታይም በሁለቱም ቡድኖች አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አልተደረገም። 72ኛው ደቂቃ ላይ የዱራሜው ወንዱ ፍሬው ወደ ሳጥን ይዞት የገባውን ኳስ ለዳግም ደሳለኝ አመቻችቶ ሲያቀብል ዳግምም ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ይህም በአጋማሹ የተሻለው የተፈጠረ የግብ ዕድል ነበር። ጨዋታውም ያለ ግብ ተጠናቋል።

በምድብ \’ለ\’ ጅማ ላይ ቦዲቲ ከተማ እና ከምባታ ሺንሽቾ የዕለቱ የመጀመሪያ ተጋጣሚ ሆነዋል። የጨዋታው መጀመሪያ አጋማሽ ቀዳሚ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ሲታይ በተቀሩት ደቂቃዎች ቦዲቲዎች የተሻለ ብልጫ አሳይተዋል። ቡድኑ በኳስ ቁጥጥር ወደ ተቃራኒ የጎል ክልል በመሄድ የተሻለ ሆኖ ሲታይ በ27ኛ እና 32ኛ ደቂቃዎች በቢንያም ታከለ እና በናትናኤል ዳንኤል የጎል ሙከራ አድርጓል። አማካዩ ምስክር መለሰ በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቢችልም የአጥቂዎቻቸው አቋቋም በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ እየሆነ የሚደርሳቸውን ኳስ ሲያመክኑ ተስተውሏል። በአንፃሩ ከምባታ ሽንሽቾዎች በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ ሆነው ታይተዋል ፤ ሆኖም በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ክልል መድረስ አልቻሉም።

\"\"

በሁለተኛ አጋማሽ ከመጀመሪያው የቀነሰ ፉክክር ታይቷል። ወደ ግብ በመድረሱ ረገድ በንፅፅር የተሻሉ የነበሩት ቦዲቲዎች 83ኛው ደቂቃ በአማኑኤል አሊሶ ቡድኑን አሸናፊ ያደረግች ብቸኛ ግብ አስቆጥረዋል።
የአየር ላይ ኳሶች በበዙበት በዚህ ፍልሚያ ከምባታ ሽንሺቾዎች የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው በቤዲቲ 1-0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ጅማ አባ ጅፋር እና ኦሜድላ ሆሳዕና ላይ የምድብ \’ሐ\’ ቀዳሚውን ጨዋታ አድርገዋል። ብዙም ሳቢ ባልነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ጅማ አባ ጅፋሮች ተሽለው የተገኙ ሲሆን ኦሜድላዎች በአንፃሩ በረጅም ኳስ እና በጥቂት ቅብብል ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክሩ ተመልክተናል። ሆኖም ሁለቱም ቡድኖች በማጥቃቱ ረገድ ሳይሳካላቸው ምንም ግብ ሳያስቆጥሩ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ተሽለው የገቡት ኦሜድላዎች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ እና በተወሰነ መልኩ ተጭነው በመጫወት ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የነበረ ሲሆን በ62ኛው ደቂቃ ያገኙትን የግብ ዕድል አላዛር ተስፋዬ አማካይነት በማስቆጠር መሪ ሆነዋል። 

\"\"

ከግቧ መቆጠር በኋላ ጅማ አባ ጅፋሮች በጥቂቱ የመነቃቃት ስሜት የታየባቸው ቢሆንም ኦሜድላዎች ያገኙትን የግብ ብልጫ ለማስጠበቅ በጥንቃቄ በመጫወት እና የጅማ አባጅ ፋርን ማጥቃት በማክሸፍ ምንም ግብ ሳያስተናግዱ ጣፋጭ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።

የ08፡00 ጨዋታዎች

ባህርዳር ላይ በምድብ \’ሀ\’ ተጠባቂው የወልዲያ እና የቤንች ማጂ ቡና ጨዋታ ሲደረግ እጅግ ብርቱ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ቤንች ማጂዎች የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ብሩክ ወልዱ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው ቴዎድሮስ ጌትነት እና የግቡ የቀኝ ቋሚ ግብ ከመሆን አግደውታል። አቦሎቹ በ20 ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ተጫዋቾችን በጉዳት ቀይረው ካስወጡ በኋላ ግን የጨዋታው ሚዛን ወደ ወልዲያ አመዝኗል። 26ኛው ደቂቃ ላይም ወንድማገኝ ሌራ ከግራ መስመር ከረጅም ርቀት ያሻማውን ኳስ ወርቁ ጌታዋ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ወልዲያን መሪ ማድረግ ችሏል። በሁለቱም በኩል ዳኝነት ላይ በሚነሱ ጥያቄዎች እየተጓዘ የቀጠለው ጨዋታ ይባስ ብሎም 44ኛው ደቂቃ ላይ ቤንች ማጂዎች ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ ተነክቷል በሚል የፍጹም ቅጣት ምት ባገኙበት ቅፅበት እጅግ ተጋግሎ ቀጥሏል። ፍጹም ቅጣት ምቱንም ኤፍሬም ታምሩ አስቆጥሮ ክለቡን አቻ ሲያደርግ በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም ራሱ ኤፍሬም ታምሩ በቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ሞክሮት የግቡ የላዩ አግዳሚ መልሶበታል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በመረጡት ጥንቃቄ በተሞላው አጨዋወት እና በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ጉሽሚያዎች በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝቶ በመድረሱ በኩል ወልዲያዎች የተሻሉ ነበሩ። 73ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም ላንቃሞ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ወደግብ የሞከረውና ግብጠባቂው መስፍን ሙዜ የመለሰበት ኳስ በአጋማሹ የተሻለው የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ቤንች ማጂ ቡናዎች  በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ዘላለም በየነ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሙሉዓለም በየነ በግንባሩ ገጭቶ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የግቡን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶበታል። ጨዋታው ዳኝነት ላይ በተደጋጋሚ በሚነሱ ጥያቄዎች አሰልቺ እየሆነ ሲሄድ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ላይ የወልዲያው ወንድማገኝ ሌራ ከቅጣት ምት ጥሩ ሙከራ አድርጎ ግብጠባቂው መስፍን ሙዜ በእግሩ መልሶበታል። ጨዋታውም 1-1 ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ቤንች ማጂ ቡና በተከታታይ ሳምንታት ይዞት የነበረውን የምድቡ መሪነት ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስረክቦ 23 ነጥቦችን በመያዝ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ይርጋ ጨፌ ቡና እና ደብረብርሃን ከተማ የምድብ \’ለ\’ የዛሬውን ሁለተኛ ጨዋታ አድርገዋል። ጨዋታው ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ ቢጀምርም ደብረብርሀኖች
ያገኟትን የመጀመሪያ ኳስ በ15ኛው ደቂቃ በያሬድ ብርሃኑ ማስቆጠር ችለዋል። ይርጋ ጨፌዎች ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ ሙሉ ለሙሉ ጨዋታውን መቆጣጠር ሲችሉ በ18ኛ እና 32ኛ ደቂቃዎች በመላሊኤል ብርሃኑ እና በብስራት ገበየው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገዋል። ደብረ ብርሀኖች በበኩላቸው በመከላከል እና በመልሶ ማጥቃት እየተንቀሳቀሱ ጨዋታውን አጋምሰዋል።

\"\"

በሁለተኛ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ፈጣን እንቅስቃሴ ታይቷል። ገና በ48ኝምው ደቂቃ ይርጋ ጨፌ ቡና በመላሊኤል ብርሃኑ ጎል አቻ ሆነዋል።
ቡድኖቹ በፈጣን ማጥቃት ወደ ጎል የሚደርሱበት እንቅስቃሴ ቀጥሎ 52ኛ ደቂቃ ላይ ዳዊት አሰፋ በራሱ ላይ ባስቆጠራት ግን ደብረ ብርሃኖች መሪ ሆነዋል። ይርጋጨፌዎች ጎል ከስተናገዱ በኋላ በየደቂቃዎች ወደ ደብረ ብርሃን የጎል ክልል በመድረስ ሙከራዎች ሲያደርጉ ቆይተዋል። በ90ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምትም በኢሳያስ ታደሰ አማካይነት አስቆጥረው ጨዋታው 2-2 ተፈፅሟል።

ሆሳዕና ላይ ቡራዩ ከተማ እና ስልጤ ወራቤን ባገናኘው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ገና በ10ኛ ደቂቃ ቡራዩ ከተማዎች በአንዋር ሙራድ አማካኝነት ግብ በማስቆጠር በጊዜ መሪ ሆነዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ስልጤ ወራቤዎች መነቃቃት የታየባቸውና ግብ ለማስቆጠር ወደ ግብ በመሄድ እና ጫና በመፍጠር ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ቡራዩ ከተማዎች በጥብቅ መከላከል የመጀመሪያ አጋማሽ ግብ ሳያስተናግዱ ጨርሰዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ስልጤ ወራቤዎች ከመጀመሪያ አጋማሽ ተሽለው በመቅረብ ጨዋታው እንደተጀመረ በ46ኛው ደቂቃ ላይ የፈጠሩትን የግብ ዕድል በሀኑሳር አወል አማካኝነት በመጠቀም አቻ መሆን ችለዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ለመሸናነፍ እና ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ቢታይም ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

\"\"

የ10፡00 ጨዋታዎች

በምድብ \’ሀ\’ የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ በጅማ አባ ቡና እና በቡታጅራ ከተማ መካከል ሲደረግ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በተደጋጋሚ በሚከሰቱ አካላዊ ንክኪዎች የደበዘዘ ነበር። በአጋማሹ የተሻለው ሙከራም በአባ ቡናዎች ሲደረግ 10ኛው ደቂቃ ላይ እስጢፋኖስ ተማም ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ብዙዓየሁ እንዳሻው ኳሱ ዓየር ላይ እንዳለ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። በእንቅስቃሴ ረገድ ካለፉት ጨዋታዎች ተሻሽለው የቀረቡት ቡታጅራዎች 20ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። ልዑል ኃይሉ ከቀኝ መስመር ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ተስፋዬ ባደርጋ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተሻሽሎ ሲቀጥል 56ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባ ቡናው ብዙዓየሁ እንዳሻው ግሩም ሙከራ ቢያደርግም የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶበታል። ጨዋታው ዳኝነት ላይ በሚነሱ ቅሬታዎች ታጅቦ በብርቱ ፉክክር ሲቀጥል ጅማ አባቡናዎች 74ኛው ደቂቃ ላይ የማሸነፊያ ግብ አስቆጥረዋል። ብሩክ ዳንኤል ከሳጥን ውጪ በአስደናቂ ሁኔታ አክርሮ የመታው ኳስ የግብ ጠባቂውን እጅ ጥሶ መረቡ ላይ አርፏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ግቡን ያስቆጠረው ብሩክ ዳንኤል ልብሱን አውልቆ ደስታውን ሲገልጽ ቢጫ ካርድ ተመልክቷል። በዚሁ አጋጣሚ \”ግብ ከማስቆጠሩ በፊት ቢጫ ካርድ ስለነበረው በሁለት ቢጫ መወገድ ነበረበት\” በሚል በቡታጅራዎች በኩል እጅግ ከፍተኛ ቅሬታ ተሰምቷል። ቡታጅራዎች እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ጨዋታውም በጅማ አባ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በምድብ \’ለ\’ አምቦ እና አዲስ አበባን ባገናኘው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በ4ኛ ደቂቃ ላይ የመዲናዋ ቡድን በኤርሚያስ ኃይሉ ጎል ቀዳሚ ሆኗል። በመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ቢኖርም በተመልካችም ዘንድ ባልተጠበቀ መልኩ በአምቦ ከተማ የጨወታ ብልጫ የተወሰደባቸው አዲስ አበባዎች በማፈግፈግ እና በመልሶ ማጥቃት ሲጫወቱ ተመልክተናል። በመጀመሪያ አጋማሽ አምቦዎች በተመልካች አድናቆት ቢቸራቸውም ግብ ሳያስቆጥሩ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

\"\"

ሁለተኛ አጋማሽ አምቦ ከተማዎች ኳስ በመጫወት ከተጋጣሚያቸው ተሽለው ሲገኙ ፈጣን በሆነ የማጥቃት እንቅስቃሴ ኳሶች በረጅም በመጣል በግራም በቀኝ ያሉ የመስመር ተጫዋቾች ለአጥቂዋቻቸው ለማድረስ ሞክረዋል። በአዲስ አበባ ጠንካራ የመከላከል ብቃት ጎል ማስቆጠር ባይችሉም በ60ኛ ደቂቃ ላይ በተገኘው ፍፁም ቅጣት ምት በነብዩ ንጉሱ የአቻነቷን ጎል አግኝተዋል። አዲስ አበባዎች ጎል ከተቆጠረባቸው ጥቂት ጊዜ በኋላ በመልሶ ማጥቃት በ64 ደቂቃ ላይ በዘርዓይ ገ/ሥላሴ መሪ መሆን ችለዋል። በተቀሩት ደቂቃዎች አምቦ ከተማዎች በግራ እና በቀኝ ባሉ የመስመር ተጫዋቾች ረጃጅም ኳሶችን በመጣል ጎል ለማስቆጠር ቢጥሩም በአዲስ አበባዎች ጠንካራ መከላከል የአቻነቷን ጎል ማስቆጠር አልቻሉም። አዲስ አበባዎች ጥብቅ በሆነ መከላከል መሪነታቸውን አስጠብቀው ጨዋታውን በአሸናፊነት አጠናቀዋል።

ደሴን ከዳሞት ባገናኘው የምድብ \’ሐ\’ የመጨረሻ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ደሴ ከተማ በተወሰነ መልኩ ተሽለው የታዩበት ጨዋታ ሲሆን ዳሞት ከተማም በጠንካራ የመከላከል አጨዋወት እና የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ተፋልሟል። በደሴ ከተማ በኩል በተስሏች ሳየመን እና በማናዬ ፋንቱ የሚመራው የፊት መስመር ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም በዳሞት ከተማ በኩል በወርቁ አዲስ የሚመራው የመከላከል ክፍል በመቋቋም ምንም ግብ ሳይቆጠር የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ በተመሳሳይ አጨዋወት የቀጠለ ሲሆን የደሴ የማጥቃት ክፍል እና የዳሞት የመከላከል ክፍል ያደረጉት ፍጥጫን ያሳየን አሳይቶናል። ሆኖም ሁለተኛውም አጋማሽም ምንም ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው ምንም ግብ ተጠናቆ ነጥብ ሊጋሩ ችለዋል።

\"\"