ከፍተኛ ሊግ | የ18ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ 11 ጨዋታዎችን ሲያስተናግድ ቤንች ማጂ ቡና እና ሻሸመኔ ከተማ ወሳኝ ድሎች አሳክተዋል።

ቴዎድሮስ ታከለ እና ጫላ አቤ

ምድብ ሀ

አሰላ ላይ የሚከናወነው የከፍተኛ ሊጉ ቀዳሚ ምድብ ዛሬ አራት ጨዋታዎችን አስተናግዷል። በቅድሚያ የተገናኙት ወሎ ኮምቦልቻ እና ሰበታ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ብሩክ ግርማ ባስቆጠረው ግብ ሰበታ ከተማን አሸናፊ አድርጓል። በውጣቱ መሰረትም ተከታታይ ድሎችን ማሳካት የቻለው ሰበታ ከወራጅነት ስጋቱ ፈቀቅ ብሎ 11ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። በመቀጠል ሀላባ ከተማ እና ጅማ አባ ቡና ጨዋታቸውን በ1-1 ውጤት ሲፈፅሙ አቡሽ ደርቤ ለሀላባ ዘላዓለም አበበ ደግሞ ለአባ ቡና አስቆጥረዋል።

\"\"

ከሰዓት በተከናወነው ጨዋታ ቤንች ማጂ ቡና በያሬድ ወንድምአገኝ የ86ኛ ደቂቃ ጎል አቃቂ ክ/ከተማን መርታት ችሏል። በዚህም ከንግድ ባንክ ቀድሞ ጨዋታውን ያደረገው ቡድኑ ተቀናቃኙን በሁለት ነጥቦች በልጦ በ39 ነጥቦች ምድቡን መምራት ችሏል። በዕለቱ የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ደሳለኝ አሎ 85ኛ ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ጎል በመታገዝ ዱራሜ ከተማን 1-0 ረቷል።

ምድብ ለ

የምድቡ የሁለተኛ ቀን የመክፈቻ ጨዋታ ጥሩ የመሸናነፍ ፉክክርን አስመልክቶን የተገባደደ ነበር።

ሁለቱን የደቡብ ክልል ቡድኖች የሆኑትን ጂንካ ከተማ እና ቦዲቲ ከተማን ባገናኘው የመጀመሪያ የጨዋታ አጋማሽ ቦዲቲ ከተማዎች ባደረጉት ፈጠን ባለ የማጥቃት ሽግግር ጎል አርቆጥረዋል። 5ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂው ቢኒያም ታከለ ላይ በሳጥን ውስጥ ግብ ጠባቂው አቤል በላይ በሳጥን ውስጥ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠችውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ቢኒያም ከመረብ አገናኝቶ ቦዲቲን ቀዳሚ አድርጓል። ጎልን ካስተናገዱ በኋላ በረጃጅም ኳሶች ምላሽ ለመስጠት ቶሎ ቶሎ ወደ ቦዲቲ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ጂንካዎች ምስጋና ፈይሳ የመጀመሪያ ሙከራ አድርጎ በሁለተኛው አጋጣሚያቸው ወደ አቻነት መጥተዋል።

\"\"

25ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጎል ማቲያስ ማዳ ሲመታ ተከላካዩ አገኘው ኩታፎ በእጁ ሳጥን ውስጥ ኳሷን በማስቀረቱ በዕለቱ ዳኛ የተሰጠችውን የፍፁም ቅጣት ምት ማኑሄ ጌታቸው ወደ 1-1 ቡድኑን አሸጋግሯል። አጋማሹ ሊገባደድ በቀሩት አስራ አምስት ደቂቃዎች ተመጣጣኝ ፉክክርን ጨዋታው ቢያሳየንም ተደጋጋሚ የተከላካይ ክፍል መዘናጋቶች የሚታይባቸውን ጂንካ ከተማዎች በዚሁ ስህተታቸውን ቢኒያም ታከለ ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ የሰጠውን ማሞ አየለ 2ለ1 ያደረገበትን ጎል አስገኝቷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲቀጥል ጂንካ ከተማዎች አመዛኙን የጨዋታ ብልጫን ወስደው የታዩበት ነበር። ለዚህም ማሳያው 57ኛው ደቂቃ የማኑሄ ጌታቸውን ጥሩ የማቀበል አቅም ተጠቅሞ መልካሙ ፉንዱሬ ጂንካን 2-2 አድርጓል። ጂንካ ከተማዎች በሌዊ ሎኛ ቦዲቲዎች በአማኑኤል ካልሳ አማካኝነት ግልፅ ዕድሎችን አግኝተው የነበረ ቢሆንም ጨዋታ በቀዳሚው አርባ አምስት በተቆጠሩ አራት ጎሎች 2ለ2 ተፈፅሟል።

በደረጃ ሰንጠረዡ አንደኛ እና ሁለተኛ ላይ የተቀመጡትን ክለቦች ያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ መሪው ሻሸመኔ ከተማን ባለ ድል አድርጎ ተቋጭቷል።

\"\"

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ባስጀመሩት የሻሸመኔ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ የ8 ሰዓት ጨዋታ በርካታ ደጋፊዎች የታደሙበትን ሁነት አስመልክቶናል። ጨዋታውን ፈጠን ባለ የመስመር ላይ የሽግግር እንቅስቃሴ ያስጀመሩት ሻሸመኔዎች ገና በጊዜ 10ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ እና መረብን አዋህደዋል። አብዱልከሪም ቃሲም የግል አቅሙን ተጠቅሞ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ያሻገረውን አሸናፊ ጥሩ በጥሩ ዕይታ ያመቻቸለትን ልማደኛው አግቢ ፉዓድ መሐመድ አስቆጥሯታል። ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ በሁለቱ ኮሪደሮች በኩል ወደ ሳጥን ሰብሮ በመግባት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ጥቃትን ለመሰንዘር የሚዳዱት አዲስ አበባዎች ከፊት ተሰልፈው የሚገኙት ሙሉቀን ታሪኩ ፣ ኤርሚስ ሐይሉ እና ሙከረም ምዕራብ ላይ በሚታዩ የመረጋጋት ችግሮች ጎሎችን እንዳያስቆጥሩ አድርጓቸው ተስተውሏል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ በእጅጉ ተሻሽለው የቀረቡት አዲስ አበባ ከተማዎች መሆን ቢችሉም የአጨራረስ ድክመታቸውን አሁንም አለመቅረፋቸው በመልሶ ማጥቃት አደረጃጀት ሲጫወቱ በነበሩት ሻሸመኔዎች ሁለተኛ ግብ ሊያስተናግዱ ግድ ብሏቸዋል። 62ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም ቃሲም በረጅሙ የደረሰውን ኳስ በአግባቡ ተቆጣጥሮ በግራ እግሩ የመታት ኳስ ናት ሳምሶን አሰፋ መረብ ላይ ልታርፍ የቻለችው። ጨዋታው ሊጠናቀቅ የመጨረሻዎቹን ሀያ ደቂቃዎች የአጥቂ ቁጥራቸው ከፍ በማድረግ በተደራጀ የጨዋታ ፍሰት ብልጫን ያሳዩት የመዲናይቱ ክለብ አዲስ አበባ 67ኛ ደቂቃ ሮቤል ግርማ ከማዕዘን ሲያሻማ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው ኤርሚያስ ሐይሉ በግንባር በማስቆጠር ወደ 2ለ1 ጨዋታውን አድርጓል። በቀሩት ደቂቃዎች አዲስ አበባ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ሙከራዎችን ቢያደርጉም የግብ ጠባቂው ታምራት ዳኜ ድንቅ ብቃት ታግዞበት ጨዋታው ሻሸመኔውን መሪ አድርጓል። በውጤቱም ሻሸመኔ ከተረታው አዲስአበባ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ስምንት አስፍቷል።

\"\"

አሰልቺ መልክን የተላበሰው የሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ በጉለሌ አሸናፊነት ተጠናቋል።

የተቀዛቀዘ የሜዳ ላይ ፉክክሮችን ያስመለከተን ጨዋታ ገና በጊዜ ከመረብ ባረፈች ጎል 1-0 ፍፃሜን አግኝቷል። 7ኛው ደቂቃ ላይ ተረፈ ተሾመ በረጅሙ ከቀኝ የሜዳው ክፍል ያሻገራትን ኳስ ልዑል ኃይለጊዮርጊስ ከመረብ አገናኝቷል። ከዕረፍት መልስ ይርጋጨፌ ቡናዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ በብስራት ገበየው እና በተለይ በአጥቂው ኦኒ ኡጁሉ አማካኝነት ጥረቶችን አድርገው የነበረ ቢሆንም ጨዋታው ከነበረው ደብዛዛነት አንፃር 1ለ0 የጉለሌ ክፍለ ከተማ የመጀመሪያ አጋማሽ ብቸኛ ጎል ተደምድሟል።

ምድብ ሐ

የካ እና ኦሜድላን ባገናኘው ቀዳሚ ጨዋታ
የመጀመሪያ አጋማሽ በ3ኛው ደቂቃ የካ ክ/ከማዎች ያገኙትን ኳስ ከመስመር በማሻገር የተገኘውን የግብ አጋጣሚ ማቲያስ ሹመቴ በጥሩ ሁኔታ በማስቆጠር መሪ መሆን ችለዋል። ከግቡ መቆጠር በኋላ የካ ክ/ከተማዎች ያገቡትን ግብ ለማስጠበቅ ወደ ኋላ አፈግፍገውና መከላከልን ምርጫ በማድረግ የተጫወቱ ሲሆን የፊት መስመራቸው ብስራት በቀለ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ሲሞክር ተመልክተናል። ኦሜድላዎች በአንፃሩ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ የሆነ ተነሳሽነት የታየባቸው ሲሆን ይህንን ተከትሎ በ45ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ደግነት ካሌብ በግንባሩ በማስቆጠር ኦሜድላን አቻ በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመሩ ማድረግ ችሏል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ ኦሜድላዎች በተሻለ መልኩ ተነቃቅተውና ጥሩ አጨዋወት ሲጫወቱ የፊት መስመራቸው ቢኒያም ጌታቸው እና ቻላቸው ቤዛ ድንቅ ጥምረት ያሳዩበት አጋማሽ ነበር። የካ ክ/ከተማዎች በጫና ውስጥ የቆዩበት እና ግብ እንዳይቆጠርባቸው ከፍተኛ የሆነ ተጋድሎ በማድረግ በሁለተኛው አጋማሽ ምንም ግብ ሳይቆጠር በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቆ ነጥብ መጋራት ችለዋል።

በሁለተኛው ጨዋታ ሀምበርቾ ዱራሜ ከ ቡራዩ ከተማ ተፋልመዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ የሀምበሪቾ ዱራሜ ፍፁም ብልጫ እና ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎች የተመለከትንበት አጋማሽ ሲሆን በአቤል ዘውዱ እና በቃልአብ ጋሻው የሚመራው የሀምበሪቾ ዱራሜ የመሀል ክፍል ጥሩ የሚባል እና የተቀናጀ ኳስ በመጫወት የግብ ዕድል ለመፍጠር ወደ ፊት ኳሶችን በማሻገር ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ተተናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ከተከላካይ ጀርባ የተላከውን ኳስ አቤል ዘውዱ ወደ ግብ በመቀየር አጋማሹን ሀምበሪቾ ዱራሜ መሪ ሆኖ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመራ አድርጓል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታው መልክ የተቀየረበት እና ቡራዩ ከተማዎች የበላይ የሆኑበት አጋማሽ ሲሆን የመሀል ክፍሉን የቀየረው አብዲ ሁሴን የተሻለ የኳስ ቁጥጥር እና ጥሩ ጥሩ ኳሶችን መስመር ላይ ለተሰለፈው ሱራፌል ተሾመ በማሻገር ግሩም ግሩም ኳሶችን ለአጥቂ ክፍሉ ለማድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በዚህ ሁኔታ በ54ኛው ደቂቃ ላይ በተፈጠረው ውዝግብ የቡራዩ ከተማ መሪ የሆነው ሙዲን ሙስጠፋ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ሆኖም ግን ቡራዩ ከተማዎች ይበልጡኑ ጫና በመፍጠር በ81ኛ ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ሙሉጌታ ካሳሁን በግንባር በማስቆጠር ቡራዩ ከተማን አቻ ማድረግ ችሏል። ጨዋታውም በአቻ ውጤት ተተናቆ ነጥብ መጋራት ችለዋል። ሀምበርቾ አሁንም ከአቻ በላይ ውጤት ማስመዝገብ ባለመቻሉ የምድቡን መሪነት መልሶ የሚረከብበትን ዕድል አምክኗል።

\"\"

በሦስተኝነት የተከናወነው የነገሌ አርሲ እና ሶዶ ከተማ ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል። የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን የጨዋታው መጀመሪያ አከባቢ ነጌሌ አርሲዎች ተጭነው ለመጫወት ሞክረዋል። ይህንንም ተከትሎ የሶዶ የተከላካይ ክፍል የሆነው ግልፅ ግብ የሆነ ኳስ በእጅ በመንካቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተ ሲሆን ብሩክ ቦጋለ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት በማብከን ነጌሌ አርሲ መሪ የሚሆንበትን ዕድል አሳልፎ ሰጥቷል። ከቀይ ካርዱ በኋላ ነገሌ አርሲዎች ሙሉ በሙሉ ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት በመጀመሪያ አጋማሽ ፍሬ ሳያፈራ ቀርቶ ወደ መልበሻ ክፍል ማምራት ችለዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሶዶ ከተማዎች የተጫዋች ቅያሬ በማድረግ የተከላካይ ክፍላቸውን በማጠናከር ግብ እንዳይቆጠርባቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ተጫውተዋል። የሶዶ ከተማ የመሀል ክፍል ከተከላካዩ ክፍል ጋር ቅርብ በመሆን ነገሌ አርሲዎች ነፃ ቦታ እንዳያገኙ ሲያደርጉ ተስተውሏል። ጨዋታውም በዚህ ሁኔታ በመጠናቀቁ ሶዶ ከተማ በጎዶሎ ተጫዋች ግብ ሳይቆጠርበት አቻ በመውጣት ነጥብ መጋራት ችሏል።

\"\"

ገላን ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ አከናውነዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ የተደረገበት እና የገላን ከተማ በኳስ ቁጥጥር የበላይ የሆነበትና የጅማ አባ ጅፋር የተከላካይ ክፍል እና ግብ ጠባቂው ከገላን ከተማ ሲሰነዘሩ የነበሩትን የግብ ሙከራዎች ሲያበክኑ ተስተውሏል። ገላን ከተሞች ኳስን ከተከላካይ ስፍራ መስርተው ለመጫወት ሲሞክሩ በተከላካይ ስፍራ ተመስገን አዳሙ እንዲሁም በመሀል ክፍሉ አፍቅሮት ሰለሞን ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ኳስን ወደ ፊት መስመር ለተሰለፉት የኋላሸት ፍቃዱ እና በየነ ባንጃው በማቀበል ጥሩ የግብ እድሎችን የፈጠሩ ቢሆንም ምንም ግብ ሳይቆጠር አጋማሹ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም በኩል አጓጊ እና አልሸነፍ ባይነት መንፈስ የታየበት ጨዋታ ሲሆን ገላን ከተማዎች ጫና ፈጥረው ቢጫወቱም ጅማ አባ ጅፋሮች በመልሶ ማጥቃት የሚያገኙትን ቦታ በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር የሚያደርጉት ጥረት ተመልክተናል ሆኖም ግን በጨዋታው ምንም ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው ተጠናቆ ሁለቱም ክለቦች አንድ አንድ ነጥብ ተጋርተው መውጣት ችለዋል። ገላን ከተማ የምድቡን መሪነት ማስፋት የሚችልበትን ዕድል ቢያባክንም አሁንም በግብ ልዩነት ከሀምበርቾ በመብለጥ አንደኝነቱን አስጠብቋል።

\"\"