የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | የ21ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ዛሬ ሲጠናቀቅ አርባምንጭ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድል ቀንቷቸዋል።

\"\"

ድሬዳዋ ከተማ 1-4 አርባምንጭ ከተማ

ረፋድ 04፡00 ላይ የድሬዳዋ ከተማ እና የአርባምንጭ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ የመጀመሪያው አጋማሽ የአርባምንጭ ፍጹም የበላይነት የታየበት ነበር። 5ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም ታምሩ ወደ ግብ ሞክራው ግብ ጠባቂዋ የመለሰችውን ኳስ ያገኘችው ትውፊት ካዲዮ ባስቆጠረችው ግብ ጨዋታውን መምራት የጀመሩት አርባምንጮች በሦስት ደቂቃዎች ልዩነትም በቤተልሔም ታምሩ አማካኝነት ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። የአዞዎቹን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመግታት የተቸገሩት ድሬዎች ከራሳቸው የግብ ክልል ተደራጅተው ለመውጣት ሲቸገሩ ይባስ ብሎም 24ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። ቤተልሔም ታምሩ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ስትመልስባት ያገኘችው መሠረት ወርቅነህ በቀላሉ ማስቆጠር ችላለች። ራሷ መሠረት ወርቅነህ ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሊያመራ የዳኛ ፊሽካ ሲጠበቅም ለራሷ ሁለተኛውን ለቡድኗ አራተኛውን ግብ አስመዝግባለች።
\"\"

ከዕረፍት መልስ ድሬዳዋ ከተማዎች እጅግ ተሻሽለው በመቅረብ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ሲወስዱ 64ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ታደለች አብርሃም ከቀኝ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ያገኘችው ፎዚያ መሐመድ ተቀይራ በገባችበት ቅፅበት በጥሩ ብቃት በግንባሯ የገጨችው ኳስ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ መረቡ ላይ አርፏል። በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው የከበዳቸው አርባምንጮች ቤተልሔም ታምሩ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ ሳትጠቀምቀት ከቀረችው ኳስ ውጪም የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረው አሳልፈዋል። ጨዋታውም በአርባምንጭ ከተማ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ይርጋጨፌ ቡና 1-1 አዳማ ከተማ

ለተመልካች አዝናኝ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች የአዳማ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ደግሞ የይርጋጨፌዎች የበላይነት የታየበት ነበር። በአጋማሹ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻለችው ሔለን እሸቱ በግራ መስመር የተገኘውን የማዕዘን ምት ሣባ ኃ/ሚካኤል አሻምታው ተከላካዮች በትክክል ሳያርቁት ቀርተው ያገኘችውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥራው አዳማ ከተማን መሪ ስታደርግ በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም በቀኙ ቋሚ በኩል ለጥቂት በወጣባት ኳስ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርባ ነበር። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው እየተመለሱ የመጡት ይርጋጨፌ ቡናዎችም ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ሲቀጥሉ በአዳማ ተከላካዮች እና በግብ ጠባቂዋ አለመግባባት ኳሱን አቋርጣ ያገኘችው ፍሬሕይወት ተስፋዬ በግንባሯ በመግጨት አስቆጥራው በአቻ ውጤት ወደ ዕረፍት አምርተዋል።
\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በሁለቱም በኩል የጠሩ የግብ ዕድሎች አልተፈጠሩም ነበር። በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ ግን የአዳማዋ ቤተል ጢባ ግሩም ሙከራ አድርጋ የግቡን የላይ አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶባታል። ይህም በአጋማሹ ብቸኛው ለግብ የቀረበ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-1 ኢትዮ ኤሌክትሪክ

10፡00 ላይ እጅግ ማራኪ በሆኑ ቅብብሎች ታጅቦ በተደረገው የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር በመጀመሪያው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ቢወስዱም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ኤሌክትሪኮች የተሻሉ ነበሩ። በአጋማሹ የተሻለው የመጀመሪያ የግብ ዕድልም 25ኛው ደቂቃ ላይ በጊዮርጊሶች ሲፈጠር አጥቂዋ ኢየሩስ ወንድሙ ከረጅም ርቀት እየገፋች በወሰደችው ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ብትገናኝም የመጨረሻ ንክኪዋ በመርዘሙ ሳትጠቀምበት ቀርታለች። ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝተው መድረስ የቻሉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች 30ኛው ደቂቃ ላይ ሕይወት ዳንጊሶ ወደ ግብ ሞክራው የግቡን አግዳሚ ገጭቶ በተመለሰው ኳስ የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲያደርጉ 41ኛው ደቂቃ ላይ በትንቢት ሳሙኤል የቅጣት ምት ኳስም ተጨማሪ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር።
\"\"

ከዕረፍት መልስ በርካታ ስኬታማ ቅብብሎችን በማድረግ ነገር ግን ሙሉ ጨዋታ በተመሳሳይ ብርታት ለመጨረስ በመቸገር የሚታወቁት እንስት ፈረሰኞች በጨዋታው እጅግ ሲቸገሩ ይህም ለኤሌክትሪኮች ጨዋታውን ቀላል እንዲሆን አድርጓል። 51ኛው ደቂቃ ላይ በዕረፍት ተቀይራ የገባችው ምንትዋብ ዮሐንስ ባስቆጠረችው ግብ ጨዋታውን መምራት የጀመሩት ኤሌክትሪኮች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በርካታ የግብ ዕድሎችን ቢፈጥሩም በግብ ጠባቂዋ በረከት ዘመድኩን መክኖባቸዋል። 56ኛው ደቂቃ ላይ ሽታዬ ሲሣይ በግራ መስመር ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ያደረገችው ግሩም ሙከራ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስባት 59ኛው እና 63ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጣሪዋ ምንትዋብ ዮሐንስ 70ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ትንቢት ሳሙኤል ያደረጓቸውን እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ግብ ጠባቂዋ በረከት ዘመድኩን እጅግ ድንቅ በሆነ ብቃት መልሳቸዋለች። በጨዋታው የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ግን በተሻለ የጨዋታ ስሜት የተነቃቁት ጊዮርጊሶች ከተመልካቾች አድናቆት ያስተረፈ በማራኪ ቅብብል የታጀበ እንቅስቃሴ ማድረግ ችለው ነበር። ጨዋታውም በኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"</a