በሁለት ክለቦች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላልፏል

የፕሪምየር ሊጉ የበላይ አካል በሁለት ክለቦች እና በአንድ ተጫዋች ላይ ጠንከር ያለ የቅጣት ውሳኔን አሳልፏል።

\"\"

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የተጠናቀቁ ሲሆን የሊጉ የውድድር አመራርና ሥነ ስርዐት ኮሚቴም በጨዋታዎች ላይ የታዩ የዲሲፕሊን ግድፈቶችን ከዳኞች እና ከጨዋታ ኮሚሽነሮች ተቀብሎ ከመረመረ በኋላ የቅጣት በትሩን ጥፋተኛ ባላቸው ላይ አሳርፏል።

ፋሲል ከነማ ሲመራ ቆይቶ በባህር ዳር ከተማ 2-1 በተሸነፈበት ጨዋታ ላይ የክለቡ ደጋፊዎች የዕለቱን ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩን ስለ መሳደባቸው ሪፖርት ስለቀረበባቸው ክለቡ የ50 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ሲጣልበት በቀይ ካርድ ከሜዳ የተወገደው የመስመር ተጫዋቹ ዓለምብርሀን ይግዛው የሦስት ጨዋታ እና የ3 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት በተመሳሳይ በሁለት ቢጫ ካርድ የተወገደው አምሳሉ ጥላሁን የአንድ ጨዋታ እና የ1 ሺህ አምስት መቶ ብር የገንዘብ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

በሌላ ቅጣት መቻል በአርባምንጭ ከተማ 2-1 ሲሸነፍ የክለቡ ደጋፊዎች በዕለቱ ዳኞች ላይ አፀያፊ ስድብ በመሰንዘራቸው ክለቡ የ50 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተወስኖበታል። በተጫዋች ደረጃ የአርባምንጩ ግብ ጠባቂ ይስሀቅ ተገኝ (በቀይ) በመውጣቱ የሀዋሳው አብዱልባሲጥ ከማል አምስተኛ ቢጫን በማየቱ እያንዳንዳቸው የአንድ ጨዋታ እና የአንድ ሺህ አምስት መቶ ብር የገንዘብ ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

\"\"