​ቻምፒየንስ ሊግ፡ ዋይዳድ ካዛብላንካ ለፍፃሜ አልፏል

የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ሲሸጋገር የሞሮኮው ሃያል ክለብ ዋይዳድ ካዛብላንካ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ከ2011 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ለፍፃሜ ያለፈበትን ውጤት በሜዳው ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ዋይዳድ የአልጄሪያውን ዩኤስኤም አልጀርን በአጠቃላይ ውጤት 3-1 በመርታት ነው ለፍፃሜ መድረስ የቻለው፡፡ 

ዋይዳድ እና ዩኤስኤም አልጀርስ ላይ ከሶስት ሳምንት በፊት ያለግብ አቻ መለያየታቸውን ተከትሎ በካዛብላንካ ያደረጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነበር፡፡ በጨዋታውም ሁለቱም ክለቦች ተመጣጣኝ ፉክክር እና ጥሩ ጨዋታ ያሳዩ ሲሆን ዋይዳድ ያገኛቸውን እድሎቹን መጠቀሙ አሸናፊ አድርጎታል፡፡

በመሐመድ አምስተኛ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ በመሃል ሜዳ የበላይነት ለመያዝ በተደረገ ፉክክር እና ለግብ የቀሩ ሙከራዎችን ያስተናገደ ጥሩ እንቅስቃሴ የታየበት ሆኖ አልፏል፡፡ በ26ኛው ደቂቃ አሽራፍ ቤንቻርጉኢ በዩኤስኤም የፍፁም ቅጣት ምት ክልል የቀኝ ጠርዝ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ዋሊድ ኤል ካርቲ አስቆጥሮ ዋይዳድን መሪ አድርጓል፡፡ በቀድሞ የቡርኪና ፋሶ አሰልጣኝ ዩኤስኤሞች በተደጋጋሚ የአቻነት ግብ ለማግኘት በመጀመሪያው አጋማሽ ያደረጉት ጥረት ያልተሳካ ነበር፡፡

በሁለተኛው 45 ሶስት ግቦች ከመስተናገዳቸው በተጨማሪ የቀይ ካርድም ተመዟል፡፡ በዋይዳድ መለያ በአመቱ መልካም እንቅስቃሴ ያሳየው መሃመድ ኦንዠም ያሻገረለትን ኳስ ቤንቻርጉኢ በግንባሩ በመግጨት በ54ኛው ደቂቃ ላይ የቡድኑን መሪነት ሲያጠናክር ከሁለት ደቂቃ በኃላ አሚን አቱቺ በሰራው ያልተገባ ጥፋት በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተሰናብቷል፡፡ የቁጥር ብልጫን ያገኙት ዩኤስኤሞች ከ56ኛው ደቂቃ በኃላ ጫናቸውን በማጠናከር ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ባለሜዳዎቹ ጨዋታውን በማቀዝቀዝ ውጤታቸውን ለማስጠበቅ ሲጥሩ ታይቷል፡፡ አዩብ አብዱላሂ ለአልጄሪያው ክለብ በ67ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥሮ ዋይዳድ ላይ ጫና ሲያሳድር በተለይ የመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች በውጥረት ታጅቦ እንዲካሄድ አድርጓል፡፡ በጨዋታው መገባደጃ ላይ ቤንቻርጉኢ በግሩም ሁኔታ አንድ ተከላካይን አልፎ ኳስ እና መረብን በማገናኘት ዋይዳድን ከ2011 በኃላ ለፍፃሜ እንዲደርስ አስችሏል፡፡ በስታዲየሙ የተገኘው ከ40ሺ በላይ የዋይዳድ ካዛብላንካ በከፍተኛ ደስታ ተውጠው ታይተዋል፡፡

ዋይዳድ ካዛብላንካ በ1992 የአፍሪካ የክለቦች ቻምፒዮን ከሆነ በኃላ በካፍ ዋንጫ በ2002 ያሸነፈው ድል በአህጉሪቱ የክለቦች ውድድር ያሸነፈው ትልቁ ስኬቱ ነው፡፡ በሁሴን አሞታ አመራርነት ክለቡ የቦቶላ ሊግ ክብሩን ከፉስ ራባት ላይ ሲያስመልስ ለቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜም መድረስ ችሏል፡፡ ተሸናፊው ዩኤስኤም አልጀር በበኩሉ ከ2015 ፍፃሜ በኃላ ለፍፃሜ መድረስ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ክለቡ አልጄሪያ ሊግ ሞቢሊስ በሶስተኛነት መጨረሱን ተከትሎ በቻምፒየንስ ሊጉ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን የማይሳተፍ ይሆናል፡፡

ዛሬ ምሽት አሌክሳንደሪያ ላይ ሃያሉ የግብፅ ክለብ አል አሃሊ የቱኒዚያውን ኤትዋል ደ ሳህልን ያስተናግዳል፡፡ ኤትዋል ሶስ ላይ በተደረገው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በአላያ ባርጉኢ እና መሃመድ አሚን ቤን አሞር ግቦች 2-1 አሃሊን መርታቱ ይታወሳል፡፡

የቅዳሜ ውጤት

ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ 3-1 ዩኤስኤም አልጀር (0-0)

የእሁድ ጨዋታ

3፡00 – አል አሃሊ ከ ኤትዋል ስፖርቲቭ ደ ሳህል (1-2) (ቦርጅ ኤል አረብ ስታዲየም)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *