​ሴካፋ ሲኒየር ቻንሌንጅ ዋንጫ የሚካፈሉ ተጋባዥ ሃገራት ታወቁ

በህዳር ወር በኬንያ አዘጋጅነት በሚካሄደር የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ ላይ የሚሳተፉ ተጋባዥ ሃገራት እየታወቁ ነው፡፡ የመካከለኛው እና ምስራቅ አፍሪካ እግርኳስ ማህበራት ኮንፌድሬሽን ከደቡባዊ አፍሪካ እግርኳስ ማህበራት ኮንፌድሬሽን (ኮሳፋ) እና ለሰሜን አፍሪካ እግርኳስ ፌድሬሽኖች ህብረት ጋር ካርቱም ሱዳን ላይ በፈረመው የመግባቢያ ሰነድ መሰረት ሁለት ሃገራት ከሁለቱ ዞኖች በሴካፋ ዋንጫ ላይ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡

እንደኬንያው የእግርኳስ ድረ-ገፅ soka.co.ke መረጃ መሰረት ዚምባቡዌ እና ሊቢያ በውድድሩ ተሳትፎ እንደሚደርጉ ሴካፋ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡ ዚምባቡዌ በሴካፋ ዋንጫ ከዚህ ቀደም ተሳትፎ በማድረግ የምትታወቅ ሲሆን ከሰሜን አፍሪካ ተጋባዥ ሃገር ሲመጣ በቅርብ ግዜያት ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ ነው፡፡ በ2010 ታንዛኒያ ባስተናገደችው የሴካፋ ዋንጫ ኮትዲቯር በመሳተፍ እስከፍፃሜ መድረስ መቻሏ የሚታወስ ነው፡፡

በ2015 ኢትዮጵያ ላይ ከተስተናገደ በኃላ ባልተካሄደው በዚህ ውድድር ከሁለቱ ተጋባዥ ሀገራት በተጨማሪ 10 የሴካፋ ዞን ሃገራት በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡ ባለሪከርድ ቻምፒዮኗ ዩጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዛንዚባር፣ ብሩንዲ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና አዘጋጇ ኬንያ እንዲሳተፉ ይጠበቃል፡፡ ውድድሩ ከህዳር 16-30/2010 እንደሚደረግ የታወቀ ሲሆን ካካሜጋ፣ ኪሱሙ እና ናኩራ ግዛቶች ላይ ይስተናገዳል፡፡

የኬንያ እግርኳስ ማህበር ፕሬዝደንት ኒክ ሙዌንዳ ሃገራችው ቻን 2018 ለማስተናገድ ያዘጋጀቻቸውን የነበሩ እንደ ናያዮ ብሄራዊ ስታዲየሚ፣ ሞይ ኢንተርናሽናል የስፖርት ማዕከል፣ ካሳራኒ፣ ኪኖሩ ስታድየም፣ ኪፕቾጌ ኬኖ ስታዲየም የሴካፋ ዋንጫ እንደማያስተናግዱ ለsoka.co.ke አስተያየታቸውን ገልፀዋል፡፡

በተያያዘ የሴካፋ ሴቶች ቻምፒየንሺፕ በሩዋንዳ እንዲሁም የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫን ብሩንዲ እንደሚያስተናግዱ ይጠበቃል፡፡ ካፍ ባወጣው አዲሱ መመሪያ መሰረት ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ለአፍሪካ 17 ዓመት በታች ዋንጫ ለማለፍ እንደማጣሪያነት ያገለግላል፡፡ ካፍ በአህጉሪቱ ያሉት ስድስት ዞኖች ከ17 ዓመት በታች ውድድር እንዲያዘጋጁ እና ውድድሮቹ እንደማጣሪያነት እዲያገለግሉ ከዞኖቹ ጋር መግባቢያ ላይ በሳምንቱ መጀመሪያ መድርሱ የሚታወስ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *