በአሜሪካ የዋልያዎቹ ጉዞ መልማዮች ዕይታ ውስጥ የገቡ ተጫዋቾች እነማን ናቸው?

በአሁኑ ሰዓት እየተሰጠ ባለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአሜሪካ ጉዞ መግለጫ ላይ በአሜሪካ ክለብ መልማዮች ዕይታ ውስጥ የገቡ ተጫዋቾች እነማን እንደሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ አሜሪካ በማቅናት የጉብኝት የወዳጅነት ጨዋታዎች አድርጎ ከትናንት በስትያ ወደ ሀገር ቤት እንደተመለሰ ይታወቃል። ይህንን ጉዞ በተመለከተ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት መግለጫ እየተሰጠ ይገኛል። በዚህ መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ-አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን በአሜሪካ ቆይታ በክለቦች መልማዮች ዕይታ ውስጥ የገቡ ተጫዋቾችን ይፋ አድርገዋል።

አቶ ባህሩ በገለፃቸው በሁለቱ ጨዋታዎች ላይ በርካታ መልማዮች (ስካውቶች) እንደተገኙ አመላክተው ከጉያና ብሔራዊ ቡድን ጋር በነበረው ጨዋታ አራት ተጫዋቾች በሁለተኛው የሎንዶን ዩናይትድ ጨዋታ ደግሞ ተጨማሪ ሌሎች ተጫዋቾች በአሜሪካው ክለብ ዲሲ ዩናይትድ መልማዮች ዕይታ ውስጥ እንደገቡ ተናግረዋል።

በዚህም ቢኒያም በላይ፣ አቤል ያለው፣ ሽመልስ በቀለ፣ ጋቶች ፓኖም፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ ረመዳን የሱፍ እና ማርከስ ቬላዶ-ፀጋዬ በልዩ ክትትል ሲታዩ እንደነበር አመላክተዋል። ከተጠቀሱት ተጫዋቾች ውስጥ ጋቶች ፓኖም እና አቤል ያለው ከዲሲ ዩናይትድ በተጨማሪ በሌላ አንድ ክለብ መልማዮች ተፈልገው እንደነበር ገልፀው አቤል በክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ውል ስላለው ጥያቄው ወደ ክለቡ እንዲሄድ አድርገን ውል የሌለው ጋቶች እዛው ቀርቶ ዕድሉን እንዲሞክር አድርገናል ብለዋል።