አዳማ ከተማ በዮሴፍ ታረቀኝ የዝውውር ጉዳይ አቋሙን አሳውቋል

የግብፁ ክለብ አረብ ኮንትራክተር ያቀረበውን ጥያቄ አስመልክቶ አደማ ከተማ ምላሽ ሰጥቷል።

ዮሴፍ ታረቀኝ ወደ ግብፅ በማቅናት ለቀናት በአረብ ኮንትራክተር ክለብ ሙከራ በማድረግ ቆይታ እንደነበረው እና ክለቡም በዮሴፍ ታረቀኝ እንቅስቃሴ ደስተኛ በመሆኑ ለማስፈረም ለዮሴፍ ህጋዊ ባለቤት ለሆነው አዳማ ከተማ በነፃ ዝውውር ማስፈረም እንደሚፈልግ ኢሜይል መላኩን ጭምር ከዚህ ቀደም በነበረው ዘገባችን ገልፀን እንደነበረ ይታወቃል።

በዚህ ጉዳይ በፍጥነት ተሰብስቦ ውሳኔ ለመስጠት በተለያዩ ምክንያቶች የዘገየው የክለቡ ሥራ አመራር ቦርድ በዛሬው ዕለት በቀረበው የነፃ ዝውውር ጥያቄ ዙርያ ውይይት በማድረግ ክለቡ አቋሙን አሳውቋል። በዚህም መሰረት አረብ ኮንትራክተር ያቀረበውን የነፃ ዝውውር ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን እና ዮሴፍን ለማስፈረም የሚፈልግ ከሆነ የውል ማፍረሻ የኢትዮጵያ 40 ሚሊየን ብር እንዲከፍል በመወሰን ለክለቡ ምላሹን በኢሜይል ልኳል።

የግብፅ ሊግ ዝውውር ሊጠናቀቅ ቀናት በቀረው በአሁን ሰዓት አረብ ኮንትራክተር የተሰጠውን ምላሽ ተከትሎ ዮሴፍን ለማስፈረም የውል ማፍረሻ ክፍሎ ያስፈርመዋል ወይስ ዝውውሩ ይቋረጣል የሚለው ይጠበቃል።