የሲዳማ ጎፈሬ ካፕ ውድድር አንድ ተሳታፊ ክለብ በመቀየር መስከረም 5 ይጀመራል

የሲዳማ ጎፈሬ ካፕ ውድድር የሚጀመርበት ጊዜ ላይ የሁለት ቀናት ሽግሽግ ሲያደርግ አንድ ተሳታፊ ክለብም ተቀይሯል።

በሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን እና ጎፈሬ አዘጋጅነት የሚከናወነው የሲዳማ ጎፈሬ ካፕ ውድድር ከመስከረም 3 ጀምሮ በሀዋሳ እንደሚከናወን መገለፁ አይዘነጋም። ውድድሩ የቀናት ሽግሽግ እንዲደረግበት ከተሳታፊ ክለቦች በቀረበ ጥያቄም መስከረም 3 እንዲጀምር ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ውድድሩ ቅዳሜ መስረከረም 5 እንዲጀምር መወሰኑን እና ለክለቦች በይፋ ምላሽ መሰጠቱ ታውቋል።

ከውድድሩ ጋር በተያያዘ አስቀድሞ የውድድሩ ተሳታፊ ክለቦች ቢለዩም ሻሸመኔ ከተማ ከውድድሩ በመውጣቱ በምትኩ ወላይታ ድቻ መተካቱ ተመላክቷል። በዚህም ሲዳማ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማ፣ መቻል፣ ፋሲል ከነማ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ ፣ ሀምበሪቾ ዱራሜ እና ወላይታ ድቻ በውድድሩ እንደሚሳተፉ ተረጋግጧል።

የውድድሩ የእጣ ማውጣት እና የመወዳደሪያ ትጥቅ ርክክብ መርሐ-ግብር ደግሞ የፊታችን ሐሙስ መስከረም 3 በሀዋሳ እንደሚከናወን ከአዘጋጆቹ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የሲዳማ ጎፈሬ ካፕ የኦንላይን ሚዲያ አጋር የሆነችው ሶከር ኢትዮጵያም ውድድሩን የተመለከቱ አዳዲስ መረጃዎችን ከስር ከስር የምታደርስ ይሆናል።