ፈረሰኞቹ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቀዋል

አስቀድመው ጥቂት ተጫዋቾችን ያዘዋወሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ዛሬ ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ቡድናቸው ቀላቅለዋል።

በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ወደ ሁለተኛው ዙር ማጣሪያ የተቀላቀሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አስቀድመው የተወሰኑ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ በመቀላቀል በርካት ያሉ የነባር ተጫዋቾቻቸውን ውል ማራዘማቸው ይታወቃል። አሁን ደግሞ ከአርባምንጭ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን ማስፈረማቸው ተረጋግጧል። ፈረሰኞቹን የተቀላቀሉት ሁለቱ ተጫዋቾች ተከላካዩ አሸናፊ ፊዳ እና አማካዩ እንዳልካቸው መስፍን ናቸው።

አሸናፊ ፊዳ ከአርባምንጭ ተስፋ ቡድን የተገኘ ሲሆን ያለፉትን ሁለት ዓመታት በአርባምንጭ ከተማ ቆይታ ማድረጉ ይታወቃል። እንዳልካቸው መስፍን በበኩሉ ከዚህ ቀደም ለአንድ ዓመት ለጋሞ ጨንጫ ሲጫወት ቆይቶ ሁለቱን ዓመታት በአርባምንጭ ከተማ ቆይታ ያደረገ ሲሆን የታላቅ ወንድሙ ሙሉዓለም መስፍንን ፈለግ በመከተል ፈረሰኞቹ ቤት መቀላቀሉ ታውቋል።

ለሁለት ዓመታት በፈረሰኞቹ ቤት ለመቆየት የተስማሙት ሁለቱ ተጫዋቾቹ በርከት ያሉ ተጫዋቾቻቸውን ላጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቦታቸው ጥሩ አማራጭ ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።