በአምላክ ተሰማ ወደ አቢጃን ያመራል

ኢትዮጵያዊው ዳኛ ለ2024ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ለሥልጠና በተጠሩ ዳኞች ዝርዝር ውስጥ ተካቷል።

የ2024 የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት በቀጣዩ ጥር ወር ላይ ለሁለተኛ ጊዜ 24 ሀገራትን በማሳተፍ ይደረጋል። በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ሀገራት በተደረጉ ማጣሪያዎች ተለይተው ከቀናት በፊት ሙሉ በሙሉ የታወቁ ሲሆን አሁን ደግሞ ካፍ ውድድሩን ሊመሩ የሚችሉ ዳኞችን ለቅድመ ሥልጠና እና ፈተና ይፋ ሲያደርግ አለም አቀፍ ዳኛ በአምላክ ተሰማ በዝርዝሩ ከተካተቱ 69 ዳኞች መካከል ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ዳኛ ሆኖ ስሙ ተካቷል።

የአፍሪካ እግርኳስ የበላይ አካል የሆነው ካፍ ከአህጉሪቱ ካሉ 14 ሀገራት ብቻ የዳኞችን ዝርዝር ለሥልጠና ከዛም ለፈተና የጠራ ሲሆን 32ቱ በዋና ዳኝነት 33ቱ ደግሞ በረዳት ዳኝነት እንዲሁም ከምሮኮ ፣ ግብፅ ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሞሪታኒያ ልምድ ያካበቱ የቫር ዳኞች ለሥልጠናው ጥሪ አድርጓል። በአስተናጋጇ ሀገር አይቮሪኮስት በቀጣዩ ወር ጥቅምት 14 በሚሰጠው በዚህ ሥልጠና ግብፅ እና አልጄሪያ ለቅድመ ሥልጠናው በርካታ ዳኞችን ያስመረጡ ሀገራት መሆን ሲችሉ ናይጄሪያ በበኩሏ አንድም ዳኛ አለማስመረጧ በሀገሪቱ እግርኳስ ፌድሬሽን ቅሬታን እንዳስነሳ መረጃዎች አመላክተዋል።

በዚህ ቅድመ ሥልጠናው ላይ ተሳተፈው ፈተናውን የሚያልፉ 35 ዳኞች በመጨረሻም የ2023ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ የመምራት ኃላፊነትን የሚያገኙ ይሆናል።