የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የዕጣ ማውጣት መርሐግብር ዝርዝር ጉዳዮች

ከመስከረም 5 ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ የሚደረገው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የዕጣ ማውጣት ፣ ለክለቦች የትጥቅ ርክክብ እና የደንብ ውይይት ሥነ ስርዓቶች በዛሬው ዕለት ተካሂደዋል።

በሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌድሬሽን እና በጎፈሬ የትጥቅ አምራች ተቋም አማካኝነት በጣምራ የሚደረገው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የዘንድሮው ውድድር የዕጣ ማውጣት መርሐግብር በዛሬው ዕለት አመሻሹን በሀዋሳ ሮሪ ሆቴል ተከናውኗል። ከመስከረም 5 እስከ 15 ድረስ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ላይ በሚደረገው ውድድር ላይ ሰባት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ተካፋይ ሲሆኑ የዩጋንዳው ኪንዳ ቮይስም በተጋባዥነት ተካቷል።

በሥነ ስርዓቱ ላይ የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ እና የጎፈሬ ትጥቅ አምራች ድርጅት ም/ል ሥራ አስኪያጅ አቶ አቤል ወንደሰን እና ሌሎች የውድድሩ ኮሚቴ አባላት የዳኞች እና ታዛቢዎች ተወካይ እንዲሁም ተሳታፊ ክለቦች ተገኝተዋል። መርሀግብሩን በመክፈቻ ንግግር የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ የጀመሩ ሲሆን የውድድሩ ተሳታፊ ክለቦች እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ ስለ ውድድሩ አጠቃላይ ገለፃን አድርገዋል።

በመቀጠል የጎፈሬ ትጥቅ አምራች ድርጅት ም/ል ስራ አስኪያጁ አቶ አቤል ወንድወሰን ጎፈሬ ትጥቆችን በማምራት ለክለቦች ከማቅረብ በዘለለ እንዲህ ዓይነት ወሳኝ ውድድሮችን እና ኤቨንቶችን በማዘጋጀት የካበተ ልምድ እንዳለው ጠቅሰው ጎፈሬ ከሀገሪቱም አልፎ በአህጉር ደረጃ ራሱን ከፍ ስለማድረጉ በንግግራቸው አመላክተዋል። በማስከተል ለውድድሩ በተዘጋጀው ደንብ ላይ ውይይቶች እና መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ንግግሮች ከተደረጉ በኋላ ጎፈሬ ለውድድሩ ተሳታፊ ክለቦች ያዘጋጀውን ልዩ የመጫወቻ ትጥቆችን አስረክቦ በመጨረሻም የዕጣ ማውጣት ሁነት ቀጥሏል።

ሁለቱን የክልሉ ክለቦች የምድብ አባት በማድረግ የጀመረው ዕጣው በምድብ ሀ – ሲዳማ ቡና ፣ ፋሲል ከነማ ፣ ኪንዳ ቮይስ እና ወላይታ ድቻ ፣ በምድብ ለ – ሀዋሳ ከተማ ፣ ድሬዳዋ ከተማ ፣ መቻል እና ወልቂጤ ከተማ ሲደለደሉ ውድድሩ የፊታችን ቅዳሜ ከቀትር በኋላ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል። በዚህም መሠረት በመክፈቻው ዕለት 07፡00 ላይ ሲዳማ ቡና ከ ወላይታ ድቻ በ9፡00 ደግሞ ፋሲል ከነማ ከዩጋንዳው ኪንዳ ቮይስ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይገናኛሉ።