በአርባምንጭ ከተማ እና በሁለቱ ተጫዋቾች ዙርያ የተፈጠረው ውዝግብ ምንድን ነው ?

ከሰሞኑ የተፈጠረው የሁለቱ ተጫዋቾች እና የአርባምንጭ ከተማ ክለብ ውዝግብ መነሻ ምክንያቱን አጣርተናል

በዚህ ሳምንት ሶከር ኢትዮጵያ ባቀረበችው ዘገባ የአርባምንጭ ከተማ ሁለት ተጫዋቾች እንዳልካቸው መስፍን እና አሸናፊ ፊዳ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጋር በዝውውር ሂደታቸው አጠቃላይ ስምምነት በማድረግ ለሁለት ዓመት በፈረሰኞቹ ቤት ለመጫወት ዝውውራቸውን አጠናቀው ነበር። ሆኖም ጉዳዩ ፌዴሬሽን ሲደርስ ዝውውሩ ሳይፀድቅ ቀርቷል።

ይህ የሆነበት ምክንያት ምን እንደሆነ ባደረግነው ማጣራት እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ እንዳልካቸው መስፍን እና አሸናፊ ፊዳ ፌዴሬሽን በተቀመጠው እና በፀደቀ ውል ኮንትራታቸው የሚጠናቀቀው ነሐሴ 30 2015 ነው። ታዲያ አርባምንጭ ከተማ ጥር ወር 2015 የሁለቱን ተጫዋቾች ውል ለማራዘም ከተጫዋቹቹ ጋር ተነጋግሮ በመስማማት ከፍተኛ የደመወዝ ማሻሻያም በማድረግ እስከ 2016 መጨረሻ ድረስ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲቆዩ ተስማምቶ ያስፈርማል።

በዚህም መነሻነት ክለቡ ያደረገውን የደመወዝ ማሻሻያ ተግባራዊ በማድረግ እስከ ተጠናቀቀው ዓመት ድረስ ሲከፍላቸው ቆይቷል። ነገር ግን በክለቡ እና በተጫዋቾቹ መካከል የውስጥ ስምምነት ይደረግ እንጂ ህጋዊ እንዲሆን ወደ ፌዴሬሽኑ በመሄድ ውሉን ክለቡ ሳይፀድቅ ቀርቷል። ውሉም ሳይፀድቅ ተጫዋቾቹ ያለፉትን ስድስት ወራት ለውስጥ ስምምነት ተገዢ በመሆን አብረው ሲሰሩ ቆይተዋል። በሁለቱ ወገን አለመስማማት የተፈጠረው ተጫዋቾቹ ‘ነሐሴ 30 2015 ውላችን አልቋል’ በማለት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስምምነት ሲፈፀሙ አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ ደግሞ ‘እስከ 2016 የውድድር ዘመን መጨረሻ የሚያቆያቸው ውል ያላቸው መሆኑ የተጫዋቾቹ ህጋዊ ባለቤት እኔ ነኝ’ በማለት ጥያቄ በማንሳቱ ነው።

ሁለቱ ተጫዋቾች ኮንትራታችን ነሐሴ 30 2015 ተጠናቋል ወደ ፈልግንበት ክለብ መሄድ እንችላለን በማለት ህጋዊ ጠበቃ በመቅጠር  ጉዳያቸውን ለፌዴሬሽኑ በማቅረብ ክርክር ውስጥ ሲገቡ በአንፃሩም አርባምንጭ ከተማ አስቀድመው ባደረግነው ስምምነት መሠረት የተጫዋቾቹ ህጋዊ ባለቤት እኔ ነኝ በማለት ለፌዴሬሽኑ የህጋዊነት ጥያቄውን አቅርቧል። በሁለቱ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፈታት የእግርኳሱ የበላይ አካል የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጉዳዩን እየተመለከተው ሲሆን በቅርቡ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።