አዳማ ከተማ ዳግመኛ የዕግድ ውሳኔ ተወሰነበት

አዳማ ከተማ የዲሲፕሊን ኮሚቴ የሰጠውን ቀነ ገደብ ተግባራዊ ባለማድረጉ በድጋሚ የዕግድ ውሳኔ ተላልፎበታል።

ከዚህ ቀደም ለአዳማ ከተማ ግልጋሎት የሰጡት አማካዩ ዮሴፍ ዮሐንስ እና የህክምና ባለሙያው አቶ ዮሐንስ ጌታቸው የሁለት ወር ደመወዝ አልተከፈለንም በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ የዲሲፒሊን ኮሚቴ ከመረመረ በኋላ በሰባት ቀናት እንዲከፈላቸው ይህ ሳይሆን ከቀረም አዳማ ከተማ በተጫዋች ምዝገባ እና ዝውውር እንዳይስተናገድ በተጨማሪም ከፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳያገኝ ውሳኔ አሳልፏ ነበር።

ሆኖም አዳማ ከተማዎች በተሰጣቸው ቀነ ገደብ ውሳኔውን ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ፌዴሬሽኑ በትናትናው ዕለት በድጋሚ ከተጫዋቾች ዝውውር መስኮት የታገዱ መሆኑን በደብዳቤ አሳውቋል።