ከፍተኛ ሊግ | ስልጤ ወራቤ አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሞ ለውድድር ይቀርባል

በከፍተኛ ሊጉ የምድብ ሀ ተካፋይ የሆነው ስልጤ ወራቤ በዝውውሩ ባደረገው ተሳትፎ ራሱን አጠናክሮ ነገ በሚያደርገው ጨዋታ የውድድር ዓመቱን ይጀምራል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ላይ የተደለደለው ስልጤ ወራቤ ለ2016 የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ኑሩ መሐመድ እየተመራ ዝግጅቱን ሲሰራ የሰነበተ ሲሆን በከፍተኛ ሊጉ ላይ የተሻለ ተፎካካሪ ሆኖ ለመገኘት በዝውውር ገበያው በመካፈል አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል።

ክለቡ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ያስፈረመ ሲሆን በዋናነት ያስፈረማቸውን ተጫዋቾችን ስንመለከት የቀድሞው የሲዳማ ቡና እና ኤሌክትሪክ ግብ ጠባቂ ፍቅሩ ውዴሳ ፣ በደቡብ ፖሊስ ፣ ሀድያ ሆሳዕና ፣ አዳማ ከተማ እና ሀምበሪቾ የተጫወተው ተከላካዩ ደሰታ ጊቻሞ ፣ በተጠናቀቀው ዓመት በይርጋጨፌ ቡና ያሳለፈው አጥቂው ሥዩም ደስታ ፣ የቀድሞው የአርባምንጭ ፣ ሀላባ እና ነቀምት ከተማ አማካይ አሰቻለው ኡታ እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከተገኘ በኋላ በጅማ አባጅፋር እንዲሁም አምና በነገሌ አርሲ ቆይታ የነበረው አጥቂው ምሰጋናው መላኩ የክለቡ አዳዲስ ፈራሚ ተጫዋቾች ናቸው።

ቡድኑ የማቲያስ ኤሊያሰ ፣ አንሳር ዐወል እና ሙከረም አህመዲንን ውል ለተጨማሪ ዓመት አራዝሟል።

ስልጤ ወራቤ ነገ 08:00 ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅን በመግጠም የውድድር ዓመቱን ይጀምራል።