ከፍተኛ ሊግ | ይርጋጨፌ ቡና በበርካታ ዝውውሮች ራሱን ገንብቷል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተወዳዳሪው ይርጋጨፌ ቡና አስራ ስድስት ተጫዋቾችን የስብስቡ አካል በማድረግ ውድድሩን ይጀምራል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ስር የተደለደለው ይርጋጨፌ ቡና በውድድሩ ላይ ራሱን ጠንካራ ተወዳዳሪ ለማድረግ ቀደም ብሎ አሰልጣኝ አላዛር መለሠን የቀጠረ ሲሆን በሙከራ እና በቀጥታ አዳዲስ አስራ ስድስት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሎ ራሱን ለውድድሩ አዘጋጅቷል።

በወላይታ ድቻ ፣ ደቡብ ፖሊስ እና ከምባታ ሺንሺቾ የሚታወቀው ግብ ጠባቂ መኳንንት አሸናፊ ፣ የአውስኮድ ግብ ጠባቂ የነበረው ቴዎድሮስ አካሉ ፣ ከአማራ ሊግ ውድድር የተገኙት የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾቹ ሐይሌ ክፍሌ ፣ አገኘሁ ብርሀኑ እና ዘመድኩን ሺርኮ ፣ ከዶሬ ላንጋኖ የመጡት ተከላካዩ ጌታያውቃል ሮማን እና አማካዩ አየነው ሠለሞን ፣ ለፍኖተ ሰላም የተጫወቱት አማካዩ በረከት ታምራት እና አጥቂው ሔኖክ ሞገስ ፣ በኮልፌ ቀሬኒዮ ቆይታ የነበረው አማካዩ ተመስገን ኃይሉ ፣ በቦዲቲ የነበረው የመስመር አጥቂው ጌታሁን ሺርኮ ፣ ከሐረር ሲቲ የመጣው አጥቂው ልዑል ኃይሉ ፣ የቀድሞው የደቡብ ፖሊስ አጥቂ ይድነቃቸው ውበቱን ጨምሮ ከአካባቢው ፕሮጀክት አማካዮቹ ካሌብ ሽብሩ አማካይ እና አቤኔዘር ዘሪሁን እንዲሁም አጥቂእ ተስፋአለም ማሩ የክለቡ አዳዲስ ተጫዋቾች ሆነዋል።

ይርጋጨፌ ቡና ነገ 10:00 ላይ ሞጆ ከተማን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በመግጠም የውድድር ዓመቱን ይጀምራል።