የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 1-1 ሻሸመኔ ከተማ

“ከመጥፎ ቀኖች እንደ አንዱ አድርጌ ነው ዛሬን የምቆጥረው” አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ

“ከዋና ዳኞች በላይ ጨዋታውን እየረበሹ ያሉት አራተኛ ዳኞች ናቸው” አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ

የሳምንቱ ቀዳሚ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና እና ሻሸመኔ ከተማ መካከል ተከናውኖ 1ለ1 በሆነ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን አድርገዋል።

አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ – ኢትዮጵያ ቡና

በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ነጥብ ስለ ተጋሩበት ጨዋታ…

“ተጋጣሚያችን እንደሚከብደን መጀመሪያም ተነጋግረን ነበር ፣ ከእንደዚህ አይነት ቡድን ጋር ስትጫወት ጥንቃቄ ይፈልጋል ፣ እንደ አጋጣሚ ሆኖ እነርሱ ቀድመውናል በጨዋታ ጎል ማግባት ችለዋል። በዛ አልነበረም አስበን የመጣነው ከዛ በኋላ ለእነርሱ ወደ ሚመች አጨዋወት ውስጥ ነበር የገባነው ፣ ትንሽ አለመረጋጋቶች ነበሩ እኛ አካባቢ ነገር ግን በስተመጨረሻ ተጫዋቾቻችን የሚችሉትን ተፋልመው አንድ ነጥብ ይዘን እንድንወጣ አድርገዋል። በዚህ አጋጣሚ ተጫዋቾቼን ማመስገን እፈልጋለሁ።”

ከወትሮ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ ተዳክመው መታየታቸው…

“መጀመሪያም ስንመጣ ተነጋግረን ነበር። ተጋጣሚያችን በሎው ብሎክ ሜዳዎችን እንደሚዘጋብን በቁጥር በዝተው ሜዳቸው ላይ እንደሚጫወቱ ለዛ የሚሆን እንቅስቃሴዎች ፣ መረጋጋቶች ያስፈልጉን ነበር ዛሬ ትንሽ እንደወትሮ መረጋጋት አልነበረም። ሁለተኛ ከአራት ቀን በኋላ ነው ጨዋታ ያደረግነው ድካሞችም ይታዩ ነበር ፣ እኛ ያሰብነው ተረጋግተን ክፍተቶችን እየፈጠርን በምናገኘው ክፍተት መሄድ ነበር ነገር ግን ጎሉ ከገባብን በኋላ እንደገና ደግሞ አማኑኤል ገና በሀያ ምናምን ደቂቃ ተጎድቶ ከወጣብን በኋላ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ አድርጎብናል። ባሰብነው ልክ አልሄደም ከመጥፎ ቀኖች እንደ አንዱ አድርጌ ነው ዛሬን የምቆጥረው።”

የአማኑኤል ዮሐንስ ጉዳት ምን ያህል የከፋ ነው…

“አሁን ያወራነው ነገር የለም ነገር ግን ሀምስትሪሚንግ እንደሆነ ነው የሰማሁት ምን ያህል እንደሚያቆየው አላውቅም ፣ የእርሱ መውጣትም በእንቅስቃሴው ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል ነገር ግን ይሄ እግር ኳስ ነው አንዳንዴ መቀበል ነው እንደዚህ ነገሮችን።”

ከጨዋታው አንፃር ውጤቱ ይገባናል ብሎ ማሰብ ይቻላል…

“ጥሩ ነበርን ምናምን የምልበት ሁኔታ አልነበረም ከወትሮው ትንሽ የወረደ እንቅስቃሴ ፣ ዕድሎችን አልፈጠርንም። ረጃጅም ኳሶችን ነበር የምንጫወተው ለእነርሱ ተከላካይ የሚመቹ ጨዋታዎችን ነበር የምንጫወተው ፣ በእንቅስቃሴ ደረጃ ትንሽ ጥሩ አልነበርንም ብዬ ነው የማስበው ምናልባትም ጠንካራ የነበረው መከላከላችን ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች የወልደአማኑኤል መውጣት ከኋላ አካባቢ የተወሰነ ክፍተት አሳይቷል ነገር ግን አሁንም አርመን እንመጣለን እግዘብሔር ይመስገን በቂ ነው።”

አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ – ሻሸመኔ ከተማ

በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች አንድ አንድ ነጥብ ስለማግኘታቸው እና ስለ ቡድኑ ለውጥ…

“መጀመሪያ ብዙ የተበላሹ ነገሮች ነበሩ ፣ የተሸናፊነት ስነ ልቦና ነበር ይሄንን ከውስጣቸው ማውጣት ያስፈልግ ነበር። ሌላው ቅርፅ አልነበራቸውም ነበር ወደፊት ስሄዱ እና ዝም ብለው በስሜት ነው የሚያጠቁት ስለዚህ በቀላሉ ይቆጠርባቸው ነበር። አንደኛ ከዛ ከተሸናፊነት ስሜት መውጣት ላይ ነበር የሰራነው ስራ ፣ ሁለተኛ ደግሞ ቅርፅ እንዲኖረው በተለይ የመከላከል አደረጃጀቱን ጥብቅ መከላከል እንዲኖረው እና በመልሶ ማጥቃት እንድንጫወት ነው። ከተወሰኑ የመሸነፍ ስሜት እየወጣን ስንሄድ በቀጣይ ወደ አሸናፊነት ስነ ልቦና እንገባለን እና ከዛ አንፃር ይሄንን ነገር ነው እየሰራን ያለነው።”

በዛሬው ጨዋታ እየመሩ በመጨረሻ ደቂቃ ጎል አቻ ስለወጡበት መንገድ እና ውጤት ያለ ማስጠበቅ ክፍተት…

“አብዛኛው ሊጉ ላይ አሁን የተቸገርነው ከዋና ዳኞች በላይ ጨዋታውን እየረበሹ ያሉት አራተኛ ዳኞች ናቸው ፣ ይነጋል እንጂ እንዳትነፋ ይል ነበረ አራተኛ ዳኛው እንደዚህ በእግር ኳስ አይባልም። የመሐል ዳኛው አለ ፣ አራተኛ ዳኛ ማለት ዳኛውን የሚረዳ እንጂ ጨዋታውን የሚመራ ነው ማለት አይደለም ግን ከዚህም በላይ ነው ሀላፊነት እየወሰዱ ያሉት እና ይሄ ትክክል አይደለም ሊስተካከል ይገባዋል እኛ ጨዋታውን ጨርሰናል ፣ የተጨማሪ ተጨማሪ ደቂቃ ተሰጥቶ ነው ጎል የተቆጠረብን ምንም ማድረግ አይቻልም ይሄንን ተቀብለን እየተቆጨን ነው ባለ ማሸነፋችን ስለዚህ ይሄ ቡድኔ ጥሩ ነው በቀጣይ ጨዋታዎች ያግዘናል ፣ ስሜቱን ወድጄዋለሁ ግን ከጨዋታው የሚገባንን ወስደናል ብዬ አላስብም ማሸነፍ ይገባን ነበር።”

ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ስለሚደረገው ጥረት…

“አሁን ባለን ነገር ከዛ ፈቅ የምንልበት ዕድል አለ ብዬ አስባለሁ።በተቻለ መጠን ሁለት ድጂት ገብተን አንደኛውን ዙር መጨረስ አለብን ፣ ከነጥብ አኳያ ቢያንስ ወራጅ ቀጠና ላይ እንኳን ብንሆን ከእኛ ከፍ ያሉ ቦታ ላይ በአንድ ነጥብ በሁለት ነጥብ ተጠግተን የምንጨርስ ከሆነ የበለጠ ተስፋ እናደርጋለን ምክንያቱም አንደኛው ዙር ካለቀ በኋላ የተወሰነ ማስተካከያዎች ለማድረግ ከአመራሮቹ ጋር እየተነጋገርን ነው ማስተካከያዎች እናደርጋለን በዕርግጠኝነት በዚህ ዓመት ሊጉ ላይ ለመቆየት ጥረት እናደርጋለን ብዬ አስባለሁ።”