ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ከሻሸመኔ ነጥብ ተጋርቷል

በሣምንቱ ቀዳሚ መርሐግብር ኢትዮጵያ ቡና እና ሻሸመኔ ከተማ 1-1 ተለያይተዋል።

በሣምንቱ የመጀመሪያ መርሐግብር ኢትዮጵያ ቡና እና ሻሸመኔ ከተማ ሲገናኙ ቡናዎች በሀዋሳ ድል በቀይ በወጣው  ወልደአማኑኤል ጌቱ ምትክ ራምኬል ጀምስ በመተካት ለጨዋታው ሲቀርቡ ከባህርዳር ጋር ነጥብ ተጋርተው በነበሩት ሻሸመኔ ከተማዎች በኩል ደግሞ ምንተስኖት ከበደ ፣ ቻላቸው መንበሩ እና ማይክል ኔልሰን ወጥተው ጌታዓለም ማሙዬ ፣ ኤቢሳ ከድር እና አብዱልቃድር ናስር ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥሩ ፍጹም ብልጫ በመውሰድ ዝግ ባለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመጫወት ሲሞክሩ ሻሸመኔዎች በአንጻሩ የሚያገኙትን ኳስ በፍጥነት ከግብ ክልላቸው በማስወጣት በጥቂት ንክኪዎች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል።

በአጋማሹ ብቸኛ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራም ሻሸመኔዎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። አብዱልቃድር ናስር ከመሃል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ የቡና ተከላካዮች በተዘናጉበት ቅጽበት ተቆጣጥሮት ግብ ጠባቂ ጋር በመገናኘት በተረጋጋ አጨራረስ ግብ አድርጎታል።

ካለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች ባልተለመደ መልኩ በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው እጅግ ተዳክመው የቀረቡት ቡናዎች ይባስ ብሎም 30ኛው ደቂቃ ላይ ወሳኙ አማካያቸውን አማኑኤል ዮሐንስን በጉዳት አጥተው በኤርሚያስ ሹምበዛ ለመተካት ሲገደዱ አንድም ለግብ የቀረበ ሙከራም ሳያደርጉ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተሻለ መነቃቃት ያሳዩት ሻሸመኔዎች 52ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲያደርጉ አሸናፊ ጥሩነህ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ አስወጥቶበታል።

ለኳስ ቁጥጥሩ ቅድሚያ በመስጠት የአቻነት ግብ ለማስቆጠር መታተራቸውን የቀጠሉት ቡናማዎች ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመግባት ሲቸገሩ 65ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ሊቆጠርባቸው ነበር። አሸናፊ ጥሩነህ እየገፋ ሳጥን ውስጥ ባስገባው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ መልሶበት ወርቃማውን የግብ ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በቀሪ ደቂቃዎችም ሁለቱም ቡድኖች መጠነኛ ፉክክር ሲያደርጉ የኢትዮጵያ ቡናዎቹ አብዱልከሪም ወርቁ እና ኤርሚያስ ሹምበዛ ከሳጥን ውጪ ሙከራ አድርገው ግብ ጠባቂው ኬን ሳይዲ ከመለሰባቸው ኳስ ውጪ ተጨማሪ የጠሩ የግብ ዕድሎች ሳይፈጠሩ ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ ሰባት የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ አምስተኛው ደቂቃ ላይ ቡናማዎቹ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ዋሳዋ ጄኦፍሪ በቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ የመሃል ተከላካዩ ራምኬል ጀምስ በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም 1-1 ተጠናቋል።