መረጃዎች | 38ኛ የጨዋታ ቀን

10ኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የሊጉ መርሃግብር የመጀመሪያ የጨዋታ ዕለት ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች በዚህ መልኩ ቀርበዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከሻሸመኔ ከተማ

የጨዋታ ሳምንቱ የመጀመሪያ መርሃግብር ጥሩ መነቃቃት ላይ የሚገኙትን ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኝ ይሆናል።

የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኋላ ሁለት ተከታታይ ድሎችን በሊጉ በማስመዝገብ ነጥባቸውን አስራ አራት በማድረስ የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች አሁን ላይ በሰንጠረዡ በ6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በገጠሙበት ጨዋታ ላይ በአመዛኙ ጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ አጨዋወት የመረጡት አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ ግን ለየት ያለ አቀራረብ ነበራቸው። በጨዋታውም የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ በቀጣይ ጨዋታዎቻቸው ተመሳሳይ አጨዋወት ሊከተሉ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።

ወጣቱ አሰልጣኝ ቡድኑን ወደ አሸናፊነት መንገድ ከመመለስ ባለፈ የተከላካይ መስመሩ ላይ በጎ ለውጦች አምጥቷል። ከዚ ቀደም በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ሁለት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ መስመር ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ግን አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዱና ያሳየው እንቅስቃሴም የዚ ማሳያ ነው።

በሊጉ የእስካሁኑ ጉዞ ሦስት ነጥቦችን ብቻ በመሰብሰብ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሻሸመኔ ከተማዎች እስካሁን ከያዙት ነጥብ ሁለቱ የተመዘገቡት በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች የመመዝገባቸው ነገር ቡድኑ አሁን ላይ ስላለበት መነቃቃት አይነተኛ ማሳያ ነው።

በመከላከሉ ረገድ በተለይ ከአሰልጣኝ ዘማርያም ሹመት በኃላ በሚታይ ደረጃ እምርታን እያሳየ የሚገኘው ቡድኑ በመጨረሻ ጨዋታ ከባህር ዳር ከተማ ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ የነበራቸው የመከላከል ጥንካሬ በጣም አስገራሚ ነበር ነገርግን ቡድኑ አሁንም በማጥቃቱ ረገድ ግቦችን ለማስቆጠር ሆነ እድሎችን ከመፍጠር አንፃር ግን አሁንም ብዙ ርቀት መጓዝ እንዳለባቸው እያስተዋልን እንገኛለን።

በነገው ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ተከላካያቸውን ወልደአማኑኤል ጌቱ ባለፈው ጨዋታ በተመለከተው የቀይ ካርድ ምክንያት የነገው ጨዋታ የሚያልፈው ሲሆን በሻሸመኔ ከተማ በኩል አማካዩ ማይክል ኔልሰን በቅጣት እንዲሁም ቻላቸው በጉዳት ለቀጣይ ሦስት ሳምንት የማይኖር መሆኑ ሲረጋገጥ ረዘም ላሉ ሳምንታት ከሜዳ የራቁት ኢዮብ እና ያሬድ ዳዊት ከጉዳታቸው በማገገም ወደ ልምምድ ቢመለሱም ለነገው ጨዋታ ዝግጁ እንዳልሆኑ ሰምተናል።

የጨዋታ ሳምንቱ መክፈቻ የሆነውን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታን ሚካኤል ጣዕመ የዓመቱ የመጀመሪያ ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት ሲመራው አዲሱ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ አሸብር ታፈሰ እና ኤፍሬም ሀይለማሪያም በረዳትነት አዲሱ የፊፋ ባጅ ባለቤት ኢንርናሽናል ረዳት ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተመድቧል።

ሲዳማ ቡና ከአዳማ ከተማ

የዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር ደግሞ መነቃቃት ላይ የሚገኘውን ሲዳማ ቡናን ከሰሞኑ የውጤት ቀውስ ውስጥ ከሚገኙት አዳማ ከተማ ጋር የሚያገናኝ ይሆናል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው መሪነት ወሳኝ ድል አሳክተው የተመለሱት ሲዳማ ቡናዎች አሁን ላይ በአስራ አንድ ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ተጋጣሚያቸው አዳማ ከተማ ደግሞ ሊጉ በተለየ ቅርፅ መካሄድ ከጀመረ በኃላ በመቀመጫ ከተማቸው የሚጫወቱ ቡድኖች አድርገው በማያቁት ጥሩ አጀማመርን ማድረግ ቢችሉም ከመጨረሻ ሦስት የሊግ መርሃግብራቸው አንድ ነጥብ ብቻ በማሳካት በአስራ ሦስት ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ሲዳማ ቡናዎች ኢትዮጵያ መድንን በረቱበት ጨዋታ ከውጤቱ በላይ ትልቅ መነጋገርያ የነበረው ጉዳይ በ2014 የውድድር ዘመን የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የነበረው እና ዘንድሮ በተለያዩ ምክንያቶች ተቸግሮ የቆየው ይገዙ ቦጋለ ወደ ግብ አስቆጣሪነት የመመለሱ ጉዳይ ነው።ይህም ዜና ሁነኛ ግብ አስቆጣሪ ለተራበው ቡድኑ አስደሳች ዜና ሲሆን በቀጣይም ተጫዋቹን ወደ ቀደመ ብቃቱ የመመለስ ጉዳይ የአሰልጣኝ ዘላለም ትልቅ የቤት ስራ እንደሚሆን ይጠበቃል።

አዳማ ከተማ በተመሳሳይ ከሰሞኑ በማጥቃቱ ረገድ ያላቸው አፈፃፀም ፍፁም ተዳክሞ እየተመለከትን እንገኛለን።በመጨረሻዎቹ ሶስት የሊግ መርሃግብሮች ሁለት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረ ሲሆን ከነገውም ጨዋታ ውጤት ይዘው ለመውጣት ይህን የማጥቃት ድክመታቸውን ማረም የግድ ይላቸዋል።

በአዳማ ከተማዎች በኩል ቻርልስ ሪባኑ ለእረፍት ወደ ሀገሩ ቢያቀናው እስካሁን ድረስ መመለስ ባለቻሉ ከነገው ስብስብ ውጭ ሲሆን አድናን ረሻድ በጉዳት እንዲሁ ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆኑ ተረጋግጧል።በአንፃሩ በሲዳማ ቡና በኩል መሉ ስብስቡ ለነገ ጨዋታ ዝግጁ መሆኑ ታውቋል።

ይህን ምሽት 12 ሰዓት ሲል ጅማሮውን የሚያደርገውን መርሃግብር ባህሩ ተካ በመሐል ዳኝነት ለዓለም ዋሲሁን እና ወጋየሁ አየለ ረዳቶች ዳንኤል ይታገሱ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተሰይመዋል።