አለን ካይዋ ወደ ሌላኛው የሊጉ ክለብ አምርቷል

በመጀመሪያው ዙር የሊጉ ውድድር በሻሸመኔ ከተማ ያሳለፈው ዩጋንዳዊ አጥቂ ወደ ሌላኛው የሊጉ ክለብ መዘዋውሩ ታውቋል።

በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት የኢትዮጵያን እግርኳስ ከተዋወቁ የውጪ ተጫዋቾች መካከል አንዱ አጥቂው አለን ካይዋ ነው። ተጫዋቹ ከክለቡ ጋር በግሉ ጥሩ የሚባል ጊዜን ሲያሳልፍ የነበረ ሲሆን የመጀመሪያው ዙር ውድድር ከተገባደደ በኋላ ግን ወደ ሀገሩ አምርቶ አልተመለሰም ነበር። ከክፍያ ጋር በተገናኛ ደስተኛ ያልነበረው ዩጋንዳዊ ተጫዋች መልቀቂያውን በመውሰድ ወደ ሌላ ክለብ ለማምራት ለክለቡ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ እንደነበረ ሲሰማ የሰነበተ ሲሆን አሁን ውጥኑ ሰምሮ ከሻሸመኔ ጋር መለያየቱ እርግጥ ሆኗል።

አራት ጎሎችን ያስቆጠረው ተጫዋቹም በአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራውን ኢትዮጵያ መድን መቀላቀሉን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።