ሀምበርቾ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል

በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የተቀመጠው ሀምበርቾ ሁለት ተከላካዮችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።


በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በማደግ እየተጫወቱ የሚገኙት ሀምበሪቾዎች ዳግም በሊጉ ለመቆየት ብርቱ ፈተና የገጠማቸው ሲሆን በአጋማሹ የዝውውር መስኮት በንቃት መሳተፋቸውን ቀጥለው ተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾች ወደ ቡድናቸው መጨመራቸው ተገልጿል።

በሀዋሳ ከተማ ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ የተጫወተው እና ባለፈው ዓመት ደግሞ በወልቂጤ ከተማ የመሃል ተከላካይ ሆኖ የተጫወተው አዲስ ዓለም ተስፋዬ እንዲሁም ደግሞ በሀዋሳ ፣ ኢኮስኮ እና በተከታታይ ሦስት ዓመታት በአርባምንጭ ከተማ በቀኝ መስመር ተከላካይ ስፍራ ላይ እስከ አለፈው ዓመት ድረስ ቆይታን ያደረገው ሙና በቀለ ቡድኑን የተቀላቀሉት ተጫዋቾች ናቸው።

ሀምበርቾዎች ባደረጓቸው 18 ጨዋታዎች አንድ ጨዋታ አሸንፈው ፣ አራት አቻ ወጥተው 13 ጨዋታዎችን በመሸነፍ በ7 ነጥቦች በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።