የዋልያዎቹ ጨዋታዎች በአንጋፋው አዲስ አበባ ስታዲየም ይደረጋሉ

በእድሳት ላይ የሚገኘው አንጋፋው የአዲስ አባባ ስታዲየም ከ40 ወራት በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ሊያስተናግድ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዓለም አቀፍ የብሄራዊ ቡድኖች ጨዋታ ማከናወኛ ወቅት የነጥብ ጨዋታ ባይኖረውም የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለማከናወን ቀጠሮ መያዙ ይታወቃል። የፊታችን ሀሙስ እና ዕሁድ ከሌሶቶ ብሄራዊ ቡድን ጋር ለሚደረገው ጨዋታም አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ በማቅረብ በዛሬው ዕለት በመሰባሰብ ልምምድ ጀምረዋል።

ጨዋታዎቹ የሚደረጉበትን ስታዲየም በተመለከተ ድረ-ገፃችን ሶከር ኢትዮጵያ ከቀናት በፊት ጨዋታዎቹ በአዲስ አበባ እንደሚደረጉ በጠቆመችው መሠረት ፍልሚያዎቹ በመዲናችን አዲስ አበባ መደረጋቸው እርግጥ ሆኗል። በዚህም ዋልያዎቹ በእድሳት ላይ በሚገኘው አንጋፋው አዲስ አበባ ስታዲየም ከሌሶቶ አቻቸው ጋር የሚጫወቱ ይሆናል።

ኅዳር 8 2013 ከኒጀር ጋር ከተደረገ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ጨዋታ በኋላም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የፊታችን ሀሙስ ጨዋታውን በስታዲየሙ የሚያደርግ ይሆናል።

በተያያዘ ዜና ጨዋታዎቹ ለተመልካች ክፍት ይሁን ወይስ በዝግ ይደረግ የሚለው ጉዳይ ይህንን መረጃ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ እንዳልተወሰነ ተመላክቷል።