የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የዋንጫ እና የደረጃ ጨዋታዎች የሚደረጉበት ቦታ ታወቀ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የየምድብ አሸናፊዎች እና ሁለተኛ የወጡ ክለቦች እርስ በርስ የሚገናኙበት የዋንጫ እና የደረጃ ጨዋታዎች የሚደረጉበት ጊዜ እና ቦታ ታውቋል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የበላይነት የሚደረገው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር በ28 ክለቦች መካከል በሁለት ምድብ ተከፍሎ እየተካሄደ እንደሚገኝ ይታወቃል። የዙሩ ውድድር ሊገባደድ ሁለት የጨዋታ ሳምንታት ቢቀሩትም ከሊጉ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያለፉ ክለቦች ከተለዩ ቀናት ተቆጥረዋል። በዚህም በምድብ ሀ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በምድብ ለ ደግሞ አርባምንጭ ከተማ አሸናፊ ሆነዋል።

ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜም የየምድቡ አሸናፊዎች ለሊጉ የዋንጫ ውድድር እርስ በርስ እንዲገናኙ በመደረጉ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አርባምንጭ ከተማ ግንቦት 18 ለዋንጫ የሚገናኙ ይሆናል። ጨዋታውም በተጠቀሰው ቀን በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከሰዓት 7 ሰዓት የሚከናወን ይሆናል። በዚሁ ዕለት የየምድቦቹ ሁለተኛ የወጡ ክለቦች ደግሞ ቀደም ብለው 5 ሰዓት ለደረጃ እንደሚፋለሙ ሶከር ኢትዮጵያ መረጃ ደርሷታል።