ታንዛኒያ የ2024 ሴካፋ ካጋሜ ዋንጫን ታስተናግዳለች

የሴካፋ ክለቦች ሻምፕዮና ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ መካሄድ እንደሚጀምር ሴካፋ ይፋ አድርጓል።

የዘንድሮውንየሴካፋ ክለቦች ሻምፕዮናን እንድታዘጋጅ ታንዛኒያ የተመረጠች ሀገር ሆናለች። ከሐምሌ 13 እስከ ሐምሌ 28 ድረስ በሚካሄደው ውድድር ዛንዚባርን ጨምሮ ከአስራ ሁለት አባል ሀገራት የተውጣጡ የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኖች እና ሌሎች አራት ተጋባዥ ቡድኖች በውድድሩ እንደሚሳተፉ ተረጋግጧል።

የሴካፋ ዋና ዳይሬክተር ጆን አዉካ ጌቾ ውድድሩ ከሁለት ዓመታት ቆይታ እንደሚካሄድ ከገለፁ በኋላ ቡድኖቹ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ፣ የካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ እና የተለያዩ የሀገር ቤት ሊጎች ከመጀመራቸው በፊት ጥሩ ዝግጅት እንዲያደርጉ የሚረዳ ጥሩ የቅድመ ውድድር ዘመን መድረክ እንደሆነ ተናግረዋል። ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ይህ ውድድር ከሁለት ዓመታት በኋላ የሚመለስ በመሆኑ ደስ እንደተሰኙ ገልፀዋል።

በ2002 ቅዱስ ጊዮርጊስ በዩጋንዳው ኤ ፒ አር ሁለት ለባዶ ተሸንፎ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀበት ውድድርም የኢትዮጵያ የተሻለው ውጤት ነው። በውድድሩ ሳልሀዲን ሰይድ ስድስት፤ አዳነ ግርማ በበኩሉ አምስት ግቦች ማስቆጠራቸው ይታወሳል።