የፉልሀም ምክትል አሠልጣኝ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከዋልያዎቹ ጋር ያደርጋሉ

ከሳምንታት በኋላ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ወሳኝ ጨዋታ ያላት ጊኒ ቢሳዎ ዋና አሠልጣኝ ተደርገው የተሾሙት ያሁኑ የፉልሀም ረዳት አሠልጣኝ በክራቨን ኮቴጅ አሸኛኘት ተደረገላቸው።

ካለንበት ወር የመጨረሻ ቀናት አንስቶ በአህጉራችን አፍሪካ የዓለም ዋንጫ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች የሚደረጉ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያም ወሳኝ ሁለት ጨዋታዎችን ከጊኒ ቢሳዎ እና ጅቡቲ ጋር ታከናውናለች። ብሔራዊ ቡድናችን በሁለት የምድብ ጨዋታዎች በድምሩ ከአንድ ነጥብ በላይ ማስመዝገብ ባለመቻሉ ከምድቡ ለማለፍ ከዚህ በኋላ ከሚደረጉት ጨዋታዎች የመጨረሻውን ነጥብ ማግኘት የግድ ይለዋል።

ግንቦት 29 ከጊኒ ጋር የሚደረገው ጨዋታ የቢሳዎ ስታዲየም በሆነው ስታዲዮ 24 ሴቴምብሮ ሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ በካፍ ፍቃድ ያለው ስታዲየም የሌላት ጅቡቲ ባስመዘገበችው የሞሮኮው ስታድ ኤል አብዲ ኤል ጃዲዳ እንደሚደረግ ከቀናት በፊት ዘገባ አቅርበን ነበር።

በመጀመሪያዎቹ ሁለት የምድቡ ጨዋታዎች ከቡርኪናፋሶው እና ጅቡቲ ጋር የተገናኘችው ጊኒ ቢሳዎ አራት ነጥብ ያገኘች ሲሆን ከላይ በጠቀስነው ቀን ከዋልያዎቹ ጋር በሜዳዋ ትጫወታለች። ከዚህ የዋልያዎቹ ጨዋታ ጀምሮም ብሔራዊ ቡድኑን እንዲያሰለጥኑ የውድድር ዓመቱን የፉልሀሙ ማርኮ ሲልቫ ረዳት አሠልጣኝ ሆነው ያሳለፉት ልዊስ ቦዋ ሞርት መሾማቸው ከሳምንታት በፊት ይፋ መሆኑ አይዘነጋም። በፉልሀም ቤት ሰባት የውድድር ዓመታትን በተጫዋችነት ሦስት የውድድር ዓመታትን ደግሞ በአሠልጣኝነት ያሳለፉት የ46 ዓመቱ ፖርቱጋላዊ እጅግ በሚወደዱበት ክራቨን ኮቴጅ የመጨረሻ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ ዘ ኮቴጀርስ በሚል ቅፅል ስም በሚጠሩት ደጋፊዎች ሞቅ ያለ አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል።

አሠልጣኙም ሹመታቸውን ከሰሙ በኋላ ከእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ስራቸው ጎን ለጎን የብሔራዊ ቡድኑን ተጫዋቾች ሲከታተሉ የነበረ ሲሆን ከቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት የመጨረሻ የሊጉ ጨዋታ በኋላ በቀጥታ ወደ አዲሱ የሙሉ ጊዜ ስራቸው ፊታቸውን አዙረው ለኢትዮጵያው ጨዋታ እንደሚዘጋጁ ተገልጿል።