የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ | የ24ኛ ሳምንት ምርጥ 11

የ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን መነሻ በማድረግ ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።

አደራደር ፡ 4-3-3

ግብ ጠባቂ

ፓሉማ ፓጁ – ሀምበርቾ

ሀምበርቾ እጅግ ደካማ ሆኖ በቀረበበት ጨዋታ መቻሎች 22 ሙከራዎችን ማድረግ ሲችሉ ከእነዚህ ውስጥ ካደረጓቸው ዘጠኝ ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ግን ሁለቱን ብቻ ነው ያስቆጠሩት። ጋናዊው ግብ ጠባቂም ምንም እንኳ ሁለት ግቦች ቢቆጠሩበትም ቡድኑ በርካታ ግቦችን አስተናግዶ አሰቃቂ ሽንፈት እንዳይቀምስ የተቻለውን ሁሉ በማድረጉ በምርጫችን ልናካትተው ችለናል።

ተከላካዮች

ሱሌይማን ሀሚድ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በ21 ጨዋታዎች በድምሩ 1678 ደቂቃዎች ተሳትፎ የተጫወተው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሱሌይማን ሀሚድ ቡድኑ ወልቂጤ ከተማን በረታበት ጨዋታ የነበረው አበርክቶ ከፍ ያለ ነበር። ከዋናው ሥራው መከላከል በተጓዳኝ በማጥቃቱ በኩል ለቡድኑ ከፍተኛ ግልጋሎት የሰጠው ሱሌይማን በምሽቱ ጨዋታ የቡድኑን ስነ ልቦና ከፍ ያደረገች የመጀመርያ ጎል ከማስቆጠሩ ባሻገር ቡድኑ በወልቂጤ በመጨረሻ ደቂቃ የደረሰበትን ከፍተኛ ጫና ተቋቁሞ እንዲወጣ በመከላከሉ ረገድ ጉልህ ድርሻ የነበረው በመሆኑ በምርጫ ውስጥ እንዲካተት ሆኗል።

ደስታ ደሙ – ሲዳማ ቡና

በጉዳት ምክንያት በሚፈለገው ልክ ግልጋሎት እንዳይሰጥ ፈተና የሆነበት ተከላካዩ በዚህ ሳምንት ያሳየው ጥሩ እንቅስቃሴው እፎይታ የሚሰጠው ይሆናል። የሳምንቱ ተጠባቂ የነበረው የሮዱዋ ደርቢ 1-1 ሲጠናቀቅ የሲዳማው የመሃል ተከላካይ ደስታ ደሙ እንቅስቃሴ የሚደነቅ ነበር። የሀዋሳን የማጥቃት ኃይል መነሻ የነበሩትን ተጫዋቾች ከመቆጣጠር ባሻገር ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ ነጥብ የተጋራበትን ጎልም ማስቆጠር ችሏል።

ፍቅሩ ዓለማየሁ – አዳማ ከተማ

ከጨዋታ ጨዋታ ራሳቸውን በተገቢው ሁኔታ በሊጉ እያስተዋወቁ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ፍቅሩ ዓለማየሁ ነው። ተከላካዩ አዳማዎች ከድሬዳዋ ከተማ ጋር 1ለ1 በተለያዩበት ጨዋታ ምንም እንኳ ድል ለማድረግ ተቃርበው የኋላ የኋላ እጅ ቢሰጡም የፍቅሩ ዓለማየሁ እንቅስቃሴ ግን ድንቅ ነበር። በተለያዩ ሚናዎች ለአሰልጣኙ የጨዋታ መንገድ ምቾትን መፍጠር የተካነው ተጫዋቹ የቡድኑን ብቸኛ ግብ አስደናቂ በሆነ ክህሎት ሁለት ተከላካዮችን አታልሎ ማስቆጠር ችሏል።

ያሬድ ካሳዬ – ኢትዮጵያ መድን

ወጣቱ የግራ መስመር ተከላካይ በጥሩ አቋም ላይ እየተገኘ ስለመሆኑ የ24ኛው ሳምንት እንቅስቃሴው አንድ ምስክር ነው። ከወገኔ ገዛኸኝ በመቀጠል በርካታ ደቂቃዎችን ሜዳ ላይ በመቆየት የኢትዮጵያ መድን ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን እያስመሰከረ የመጣው የመስመር ተከላካዩ ቡድኑ ጊዮርጊስን 1ለ0 ሲያሸንፍ ካደረገው ጠንካራ እንቅስቃሴ ባሻገር ብሩክ ሙሉጌታ ላስቆጠራት ግብም አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

አማካዮች

ፉዓድ ፈረጃ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በ17 ጨዋታዎች በድምሩ 827 ደቂቃዎችን ተሳትፎ የተጫወተው አማካዩ ፉዓድ ፈረጃ አሁን ከጨዋታ ጨዋታ በቡድኑ ውስጥ አስፈላጊ ተጫዋች እየሆነ መጥቷል። ለመጀመርያ ጊዜ ዘጠና ደቂቃውን ጨርሶ በወጣበት እና በስሙ የመጀመሪያ ጎል ባስመዘገበበት በምሽቱ የወልቂጤ ከተማ ድል የቡድኑን ወሳኙን ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር ክለቡ ወደ ዋንጫ በሚያደርገው ግስጋሴ ከነበረው ተፅዕኖ አንፃር በምርጥ አስራ አንድ ስብስብ ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።

አብዱልከሪም ወርቁ –  ኢትዮጵያ ቡና

በዘንድሮ ዓመት ከቡናማዎቹ ጋር በ22 ጨዋታዎች በድምሩ 1788 ደቂቃዎች ተሳትፎ የተጫወተው ትንሹ ቅመም አብዱልከሪም ወርቁ ቡድኑ ወላይታ ድቻን ድል ሲያደርግ ድንቅ ምሽትን አሳልፏል። በሜዳ ላይ በሚያደርጋቸው ግሩም እንቅስቃሴዎቹ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ የሚገኘው አብዱልከሪም ቡድኑ ወሳኝ ድል ሲያሳካ ለተቆጠሩት ሁለት ጎሎች ዋና ተሳታፊ የነበረው እርሱ ነው። በተለይ ለሁለተኛው ጎል መቆጠር እጅግ የተመጠነ ኳስ ያቀበለበት መንገድ አስደናቂ ነበር።

ሽመልስ በቀለ – መቻል

ባለ ብዙ ልምዱ አማካይ በመቻል ቤት እየሰጠው ያለው አገልግሎት ቡድኑ ከዓመታት በኋላ በዋንጫው ፉክክር ውስጥ እንዲኖር አድርጎታል። መቻሎች 22 ሙከራዎችን አድርገው አንድም ሙከራ ሳይደረግባቸው ሀምበርቾን 2-0 ሲያሸንፉ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻለው ሽመልስ በቀለ የቡድኑን የማሸነፊያ ግቦችም በቅጣት ምት እና በጥሩ የቡድን ጨዋታ ማስቆጠር ችሏል።

አጥቂዎች

ተመስገን ብርሃኑ – ሀዲያ ሆሳዕና

ሀዲያዎች ከሦስት ዓመት በፊት አስራ አምስት ተጫዋቾች ቡድኑን ላለማገልገል መወሰናቸውን ተከትሎ ተመስገን ድንገት ከተስፋ ቡድን ተጠርቶ ወደ ዋናው ቡድን ካደገበት ጊዜ አንስቶ ዕድገቱ ከፍ እያለ መጥቷል። ነብሮቹ ሻሸመኔ ከተማን 3ለ1 አሸንፈው ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ሲታረቁ የመስመር አጥቂው እንቅስቃሴ ግሩም ነበር። የቡድኑን የመጀመሪያ ሁለት ግቦችም በጥሩ የማጥቃት ሽግግሮች ማስቆጠር ችሏል።

ብሩክ ሙሉጌታ – ኢትዮጵያ መድን

የመስመር አጥቂው ምንም እንኳን ዓምና በነበረው አቋም ባይገኝም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ራሱን  ወደ ቀድሞ አቋሙ ለመመለስ እየተጋ ይገኛል። ኢትዮጵያ መድኖች ተከታታይ አራተኛ ድል ሲያሳኩ የቀድሞ ብቃቱን ለማግኘት እየታተረ የሚገኘው ብሩክ መልካም እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል። የቡድኑን ብቸኛ የማሸነፊያ ጎል ያስቆጠረው ብሩክ በጨዋታ ሳምንቱ ከታዩ የመስመር አጥቂዎች አንጻር ውጤታማነቱን መነሻ አድርገን ልናካትተው ችለናል።

መስፍን ታፈሰ – ኢትዮጵያ ቡና

ከባለፈው ዓመት አንፃር ዘንድሮ በሜዳ ውስጥ ከፍተኛ መነቃቃት እያሳየ የሚገኛው ፈጣኑ የመስመር አጥቂው መስፍን ታፈሰ ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ ወሳኝ ድል ሲያሳካ የነበረው ሚና የላቀ ነበር። ቡናማዎቹን ወደ ጨዋታ የመለሰች የአቻነት ጎል በሚገርም ዝላይ በግንባሩ በመግጨት ያስቆጠረው መስፍን ከጎል ማስቆጠር ባሻገር ሌሎች ለጎል የቀረቡ ሙከራዎችን በማድረግ ድንቅ ምሽትን አሳልፏል።

አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ – ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡናዎች ከመመራት ተነስተው በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ግቦች ወላይታ ድቻን 2ለ1 በመርታት ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ድል ሲቀዳጁ አሰልጣኙ ከዕረፍት መልስ ቡድናቸውን ያቀረቡበት መንገድ አድናቆት የሚያስቸር ነበር። ምንም እንኳ የተጋጣሚው ቡድን የመሃል ተከላካይ ናትናኤል ናሴሮ በሁለት ቢጫ ከሜዳ መወገዱ የተሻለ መነሳሳት ቢፈጥርላቸውም ከዚህ አጋጣሚ በፊት እና በኋላ እጅግ አስፈሪ የማጥቃት እንቅስቃሴ አድርገው ድል በመቀዳጀታቸው አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችንን ለመምራት ከአሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ ጋር ተፎካክረው ተመራጭ ሆነዋል።

ተጠባባቂዎች

አቡበከር ኑራ – ኢትዮጵያ መድን
ብርሃኑ በቀለ – ሲዳማ ቡና
በረከት ሳሙኤል – ሀዋሳ ከተማ
ኢያሱ ለገሠ – ድሬዳዋ ከተማ
መሳይ አገኘሁ – ባህር ዳር ከተማ
ታፈሰ ሰለሞን – ሀዋሳ ከተማ
ብዙዓየሁ ሰይፉ – ወላይታ ድቻ
ዳዋ ሆቴሳ – ሀዲያ ሆሳዕና
ማይክል ኪፖሩል – ሲዳማ ቡና