ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ወልዲያ በሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ የ25ኛ ሳምንት ሦስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰዓት ዛሬ ሲደረጉ ነቀምት ከተማ ድል ሲቀናጅ ወልዲያ በሊጉ መቆየቱን እውን ሆኗል ፤ የአዲስ አበባ እና ኮልፌ ጨዋታ ደግሞ ያለ ጎል ተቋጭቷል።

በቀጣዩ የውድድር ዘመን በከፍተኛ ሊጉ ላይ መቆየት የሚያስችል ውጤትን ለማሳካት ወሳኝ የነበሩ የ25ኛ ሳምንት ሦስት ጨዋታዎች ዛሬ በሦስት የተለያዩ ሜዳዎች ተደርገዋል። ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ግብርና ኮሌጅ ሜዳ ላይ ሀላባ ከተማን ከወልዲያ ያደረጉት ጨዋታ አምስት ግቦችን አስመልክቶን በመጨረሻም ወልዲያን በሊጉ ያቆየ ውጤት ተመዝግቦበት ተቋጭቷል። ጨዋታው እንደተጀመረ ገና 4ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ የሜዳው ክፍል የደረሰውን ኳስ ፋሲል አበባየሁ ከሳጥኑ ጠርዝ አስደናቂ ጎልን በማስቆጠር ሀላባን መሪ ማድረግ ችሏል።

ጨወታው በሂደት ተመጣጣኝ ፉክክርን እያስመለከተን ልክ 19ኛው ደቂቃ ላይ እንደደረሰ በጣለው ከባድ ዝናብ ለ30 ያህል ደቂቃዎች ተቋርጦ ከቆየ በኋላ ዳግም ሲመለስ 30ኛው ደቂቃ ፀጋ ማቲዮስ በረጅሙ የደረሰችውን ኳስ በአግባቡ በመቆጣጠር ከመረብ አገናኝቶ ወልድያን ወደ አቻነት አምጥቷል። ጨዋታው ከዕረፍት ተመልሶ ሲቀጥል ወልዲያዎች ብልጫውን ወስደው በተንቀሳቀሱበት ቅፅበት 47ኛው ደቂቃ የቀኝ ተከላካዩ መስቀሉ ለቴቦ ከያሬድ ወንድማገኝ የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት መረቡ ላይ ኳሷን አሳርፏታል።

ጎል ካስተናገዱ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያላመነቱት ሀላባዎች ፋሲል አበባየሁ የግብ ጠባቂው ስንታየሁ ታምራትን የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ተጠቅሞ ባስቆጠራት ግብ ጨዋታው 2ለ2 ሆኗል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ላይ 90+2 ላይ ጨዋታው እንደደረሰ በሳጥኑ ጠርዝ ያገኙትን የቅጣት ምት ወልድያዎች በቢኒያም ላንቃሞ አማካኝነት በማስቆጠር ጨዋታውን 3ለ2 አሸንፈው ወጥተዋል። ከጨዋታው መቋጫ በኋላ የሀላባ ከተማው አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር ሦስተኛዋን ግብ ቡድናቸው ሲያስተናግድ የዕለቱ ዳኛ በድለውናል በሚል በነበረ አለመግባባት የቀይ ካርድ ሰለባ ሆነዋል።

ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ላይ ነቀምቴ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋርን ባገናኘው ጨዋታ በሁለተኛው ዙር አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀምን ከቀጠሩ በኋላ በእጅጉ መሻሻሎች በታየባቸው ነቀምት ከተማዎች የበላይነት ተጠናቋል። ጨዋታውን ነቀምት ከተማ 3ለ1 ሲያሸንፍ የድል ግቦቹን ተመስገን ዱባ ፣ ገመቺስ አማኑኤል እና ልማደኛው አጥቂ ኢብሳ በፍቃዱ ሲያስቆጥሩ በሊጉ ለመቆየት የቀጣይ ጨዋታን ውጤት የሚጠብቀውን ጅማ አባጅፋር ብቸኛ ጎልን ነቢል አብዱሰላም ከመረብ አገናኝቷል።

ሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ አዲስ አበባ ከተማ ከኮልፌ ቀራኒዮ ጋር ያደረጉት ጨዋታ በሙሉ የጨዋታ ደቂቃ ጎል ሳይቆጠርበት 0ለ0 ተጠናቋል።

ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ከኳስ ቁጥጥር ጋር ባስመለከተው በዚህ ጨዋታ ኮልፌ ቀራኒዮ ላለመውረድ በሚያደርገው ብርቱ ፉክክር ከተጋጣሚው በላይ በግብ ሙከራዎች ተሽለው በመገኘት የግብ ማግባት ሙከራዎችን ሲያደርጉ ቢስተዋሉም በደካማ አጨራረስ ኳሶችን ሲያመክኑ ለመመለከት ተችሏል። የደረጃ እንጂ የመውረድ ስጋት የተለለበት አዲስ  አበባ ከተማ በመልሶ ማጥቃት ሙከራዎችን አድርገዋል። ሆኖም ግን ሳያስመለከት የመጀመሪያው አጋማሽ ተገባዷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ ኮልፌ ቀራኒዮ ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ለማስቆጠር ጠንከር ብለው ተጭነው ተጫውተዋል። አዲስ አበባ ከተማም ግብ እንዳይቆጠርበት በመከላከል ረገድ ጠንካራ ሆኖ ሁለተኛውን አጋማሽ ማሳለፍ ችሏል። ኮልፌ ቀራኒዮ ያለቁ ኳሶችን ቢያገኙም በተደጋጋሚ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው ያለግብ ተገባዷል።