መረጃዎች | 99ኛ የጨዋታ ቀን

የ25ኛ የጨዋታ ሳምንት የመክፈቻ መርሃግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ይቀርባሉ።

ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ መርሃግብር በውጤት አልባ ጉዞ ላይ የሚገኙትን ወላይታ ድቻዎችን ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያገናኛል።

ከመጨረሻ ስድስት የሊግ ጨዋታዎች በአራቱ የተሸነፉት ወላይታ ድቻዎች በተለይ በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ የ2-1 ውጤት ሲሸነፉ በሜዳ ላይ የነበራቸው እንቅስቃሴ ከወትሮው አንፃር አመርቂ አልነበረም ፤ በሁለቱም ጨዋታዎች ቡድን በሁለተኛው አጋማሽ በተጋጣሚዎቹ ፍፁም ብልጫ ተወስዶበትም እንዲሁ አስተውለናል።

የአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹው ስብስብ በተለይ በ8 ግቦች የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ቢኒያም ፍቅሬ በቅጣት እና በአቋም መውረድ ለመጨረሻ ጊዜ ለቡድኑ ግብ ካስቆጠረ ስምንት ጨዋታዎች የመቆጠራቸው ጉዳይ ለቡድኑ ሰሞነኛ መንሸራተት እንደ ምክንያት የሚቀርብ ጉዳይ ሲሆን በዚህ ሂደት ውስጥ ግን በተለይ ከአማካዩ ብዙዓየሁ ሰይፈ እና የመስመር አጥቂው ዘላለም አባተ የግል ጥረት ባለፈ የቡድኑ የማጥቃት ሀይል ፍፁም ተዳክሞ እየተመለከትን እንገኛለን።

ከማጥቃቱ ባልተናነሰ በመከላከል አወቃቀሩ ላይም ከሰሞኑ በተለይ እየተመለከትናቸው የምንገኛቸው መጠነኛ የአደረጃጀት ሆነ ግለሰባዊ ስህተቶች እንዲሁ መታረም ይገባቸዋል።

በ28 ነጥቦች በሰንጠረዡ 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች በነገው ጨዋታ ረዘም ላለ ጊዜ በጉዳት ከስብስቡ ከራቁት መልካሙ ቦጋለ እና ፀጋዬ አበራ በተጨማሪ ናትናኤል ናሴሮን በቅጣት ሲያጡ ዘላለም አባተ እና ኬኔዲ ከበደ የመሰለፍ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።

ከተከታያቸው መቻል በሦስት ነጥቦች ልቀው አሁን ላይ በ50 ነጥቦች በሰንጠረዡ አናት ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በታሪካቸው የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ፕሪምነር ሊግ ዋንጫን ለማሳካት የነገን ጨምሮ ቀሪ ስድስት የፍፃሜ ጨዋታዎች ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ይሆናል።

ወደ ሊጉ ባደጉበት ዓመት የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እየተንደረደሩ የሚገኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በንፅፅር በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ወላይታ ድቻን እንዲሁም በ29ኛ ሳምንት ሻሸመኔ ከተማን ከሚገጥሙበት ጨዋታ ውጭ ሌሎች ቀሪ መርሃግብሮቻቸው በወረቀት ደረጃ እጅግ ፈታኝ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

በሊጉ ከነጥብ ባለፈ ብዙ ጨዋታዎችን በማሸነፍ(15) ፤ ከፍተኛ ግቦችን በማስቆጠር(44) ቀዳሚ የሆኑት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በእጃቸው ያለውን የሦስት ነጥብ ልዩነት በማስጠበቅ የሊጉን ክብር ለመቀዳጀት ከፍ ባለ ጥንቃቄ እንደሚጓዙ ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል በዚህ የውድድር ዘመን ሰባት ግቦችን በማስቆጠር የቡድኑ ሁለተኛ ከፍተኛ አስቆጣሪ የሆነውን አዲስ ግደይን በነገው ጨዋታ በአምስት ቢጫ መነሻነት የማያሰልፉ ይሆናል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ዘጠኝ ጊዜ የግንኙነት ታሪክ ያላቸው ሲሆን ወላይታ ድቻዎች በሦስት ጨዋታዎች ሲረቱ ንግድ ባንኮች ሁለት ጊዜ እንዲሁም ቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተቋጭተዋል። ወላይታ ድቻ 10 ሲያስቆጥር ንግድ ባንክ በአንፃሩ 7 አስቆጥሯል።

ፋሲል ከነማ ከ ወልቂጤ ከተማ

የምሽቱ መርሃግብር ደግሞ ማሸነፍን አጥብቀው የሚሹትን ፋሲል ከነማ እና ወልቂጤ ከተማን እርስ በእርስ ያገናኛል።

በ37 ነጥቦች በሰንጠረዡ 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች በመጨረሻ ካደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉት አንዱን ብቻ ሲሆን ይህም በሰንጠረዡ ስፍራቸውን እንዲነጠቁ እና ወደታች እንዲሸራተቱ አስገድዷል።

ከተጠበቀባቸው አንፃር አማካይ የሚባልን የውድድር ዘመንን እያሳለፉ የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች በቀሪዎቹ ጨዋታዎች ከበላዮቻቸው ከሚገኙ ቡድኖች ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት አጥበው በሰንጠረዡ የተሻለ ስፍራ ይዘው ለማጠናቀቅ ያልማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በአንፃሩ በ16 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች አሁን ባለው ሁኔታ 15ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሻሸመኔ ከተማ በሦስት ነጥቦች ርቀው ተቀምጠዋል።

በ2011 የውድድር ዘመን ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደጉ በኋላ ምናልባት ወርደው በጥሎ ማለፍ ውድድር ዳግም ከተመለሱበት የውድድር ዘመን ቀጥሎ እጅግ አስከፊ የሚባል ጊዜን እያሳለፉ የሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች በዘንድሮው የውድድር ዘመን እስከአሁን ሦስት ጨዋታዎችን ብቻ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን በመጨረሻ አራት የሊግ ጨዋታዎች ተከታታይ ሽንፈት የማስተናገዳቸውም ጉዳይ ለአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት እረፍት የሚሰጥ ጉዳይ አይደለም።

በመሆኑም አሰልጣኝ ሙሉጌታ በበርካታ ከሜዳ ውጭ ባሉ ጉዳዩች የተወጠረውን ስብስባቸውን በተከታታይ ሽንፈቶች ከሚመጣው የስሜት መቀዛቀዝ ስብስባቸውን በፍጥነት ማላቀቅ የግድ ይላቸዋል።

በዐፄዎቹ በኩል ረዘም ላለ ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኙት አማኑኤል ገብረሚካኤል ፣ አፍቅሮተ ሰለሞን እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በተጨማሪ የእዮብ ማቲያስ እና የሽመክት ጉግሳ መሰለፍ አጠራጣሪ ሲሆን የወልቂጤ ከተማው ግብ ጠባቂ ፋሪስ አለዊ ቅጣት ላይ ይገኛል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ከዚህ ቀደም ሰባት ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል አራት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ያለ ጎል አቻ ተለያይተው አንድ ጨዋታ ወልቂጤ አሸንፏል። በጨዋታዎቹ ፋሲል አምስት ወልቂጤ ደግሞ ሁለት ጎሎችን አስቆጥረዋል።