የዋልያዎቹ ተጋጣሚ የልምምድ ጨዋታ አድርጋለች

የፊታችን ሀሙስ ኢትዮጵያን የምትገጥመው ጊኒ ቢሳዎ በሜዳዋ የልምምድ ጨዋታ ስታደርግ ለሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችም ጥሪ አቅርባለች።

በአሠልጣኝ ልዊስ ቦዋ ሞርት የምትመራው ጊኒ ቢሳዎ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከኢትዮጵያ እና ግብፅ ጋር ላለባት ጨዋታዎች በዚህ ሳምንት ዝግጅት የጀመረች ሲሆን በትናንትናው ዕለትም ኢንተርናሽናል ስፖርትስ ዩኒየን ኦፍ ቢሳዎ (UDIB) ጋር የልምምድ ጨዋታ አድርጋለች።

በጨዋታው ዩ ዲ አይ ቢ በአጥቂያቸው ባካሪ አማካኝነት ቀዳሚ የነበሩ ቢሆንም ኤልቪስ ባልዴ የኋላ ኋላ ብሔራዊ ቡድኑን አቻ አድርጓል። አሠልጣኝ ልዊስ ቦዋ ሞርት እስከ ትናንት ድረስ ልምምድ እያሰሯቸው ከነበሩ አስራ ስድስት ተጫዋቾች ከጆናስ ሜንዴስ ውጪ አስራ አምስቱን በጨዋታው መጠቀማቸው ተጠቁሟል።

ከቡድኑ ጋር በተያያዘ ዜና ልዊስ ቦዋ ሞርት ለሁለት በሀገር ውስጥ ሊግ እየተጫወቱ ለሚገኙ ወጣት ተጫዋቾች ጥሪ አቅርበዋል። በሀገሪቱ ናሽናል ሻምፒዮንሺፕ እየተሳተፈ ከሚገኘውና በትናንትናው ዕለት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የልምምድ ጨዋታ ካደረገው ዩ ዲ አይ ቢ የተመረጡት ሉካስ እና ባካሪ ናቸው። መጀመሪያ ጥሪ ከቀረበላቸው ተጫዋቾች መካከል አንዳንዶቹ ጉዳት እያስተናገዱ መሆኑን ተከትሎ አሠልጣኙ ከዚህ ቀደም ለተጨማሪ ተጫዋች ጥሪ ማድረጋቸው አይዘነጋም።

የጊኒ ቢሳዎ አሠልጣኝ ልዊስ ቦዋ ሞርት በዛሬው ዕለት ለተጫዋቾች ዕረፍት በመስጠት ልምምድ የማያሰሩ መሆኑ ከስፋራው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።